መረጃዎች| የ31ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

መረጃዎች| የ31ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 31ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀመሩ የዕለቱን መርሐ ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ !

 

07፡00 | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መቐለ 70 እንደርታ

ካለፉት 3 ጨዋታዎች 1 አቻ እና 2 ሽንፈት ያስተናገዱት ጊዮርጊሶች ከወራጅ ቀጠናው በ2 ነጥቦች ብቻ ርቀው 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ከ25ኛ እስከ 28ኛ ሳምንት በተካሄዱ 4 ጨዋታዎች 10 ነጥቦችን መሰብሰብ ችለው የነበሩት ፈረሰኞቹ በተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ለማስቆጠር መቸገራቸው ውጤት እንዲርቃቸው ምክንያት ሆኗል። ቡድኑ በመጀመሪያው ዙር በአቤል ያለው ፣ በሁለተኛው ዙር በፍጹም ጥላሁን ጥገኛ እንደሆነ በሚያመለክት እንቅስቃሴ እየተጓዘ ሲሆን በዛሬው ጨዋታ ፍጹም ጥላሁን በቅጣት አለመኖሩ ደግሞ ነገሩን ይበልጥ የሚያከፋባቸው ይሆናል።

ከተከታታይ ድሎች በኋላ ከሀዲያ ጋር ነጥብ ተጋርተው በአርባምንጭ የተሸነፉት መቐለ 70 እንደርታዎች በ30 ነጥቦች 19ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በሊጉ ከአርባምንጭ (5) ቀጥለው ዝቅተኛውን የማሸነፍ ቁጥር (6) የያዙት ምዓም አናብስት በሜዳ ላይ ያላቸውን እንቅስቃሴ ወደ ውጤት መመለስ የማይችሉ ከሆነ በሊጉ የመቆየታቸው ነገር አጠራጣሪ ይሆናል። በመሆኑም በዛሬው ጠንካራ ጨዋታ አሸናፊ ለመሆን ብርቱ ፍልሚያ የሚጠብቃቸው ይሆናል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ፍጹም ጥላሁን በቅጣት ምክንያት የማይኖር ሲሆን መቐለዎች አሸናፊ ሀፍቱ ፣ ፍጹም ዓለሙ ፣ ጊት ጋትኮች እና ቢኒያም ተስፋይን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 7 ጊዜ ሲገናኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ 2 ጊዜ መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ 1 ጊዜ ድል አድርገዋል፤  በአራት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹም ፈረሰኞቹ 5 ፣ ምዓም አናብስት ደግሞ 4 ግቦች ማስቆጠር ችለዋል። (በ2012 የተሰረዘውን ጨዋታ አያካትትም)

09፡00 | አዳማ ከተማ ከ ሽረ ምድረገነት

ከመጨረሻ 10 ጨዋታዎች 4 የአቻ እና 6 የሽንፈት ውጤቶችን ያስመዘገቡት አዳማዎች ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ብቻ ርቀው በ35 ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ቡድኑ ከመጨረሻ 4 ጨዋታዎች 1 ግብ ብቻ ማስቆጠር የቻለ ሲሆን በራስ መተማመኑን መልሶ ለማግኘት ድል ማሳካት ይኖርበታል። በሜዳው እና በደጋፊዎቹ ፊት ለመጫወት ዕድል ያገኘው ቡድኑ ያንን ወደ ውጤት ቀይሮ የተደላደለ ቦታ ካልተቀመጠ ካሰበው በተቃራኒው ላለመውረድ በሚደረገው ትንቅንቅ ውስጥ ራሱን ሊያገኝ ይችላል።

ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ኤሌክትሪክን 1ለ0 በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱት ሽረዎች በ33 ነጥቦች 18ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ከፋሲል ከነማ እና ድሬዳዋ ከተማ እኩል የሊጉን ዝቅተኛ የግብ መጠን (19) ያስቆጠረው ቡድኑ የፊት መስመሩን አጠናክሮ ወደ ድል ለመመለስ በዛሬው ጨዋታ በተመሳሳይ የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ ካለው አዳማ ከተማ ጋር ወሳኝ ፍልሚያ ይጠብቀዋል።

አዳማ ከተማዎች መናፍ ዐዎልን በቅጣት ምክንያት የማያሰልፉ ሲሆን በሽረ በኩል ቅጣት ላይ ካለው ሽመክት ጉግሳ ውጪ ሌሎቹ ተጫዋቾች ዝግጁ ናቸው።

በግቦች የተንበሸበሸ የግንኙነነት ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 5 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ ከተማዎች 3 ጊዜ ድል ሲያደርጉ ምድረ ገነት ሽረዎች በበኩላቸው 1 ጊዜ ማሸነፍ ሲችሉ አንድ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በግንኙነቱ አዳማ ከተማ 11 ምድረ ገነት ሽረ ደግሞ 6 ግቦች አስቆጥረዋል።

10፡00 | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሀዋሳ ከተማ

ከተከታታይ 3 የአቻ ውጤቶች በኋላ በወላይታ ድቻ 1ለ0 የተረቱት ነብሮቹ በ35 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ማስተናገዱ ፈተና ሆኖ የቀጠለበት ሀዲያ በአንድ ነጥብ ብቻ ከሚርቅበት ወራጅ ቀጠና ለመውጣት የዛሬውን ድል አብዝቶ ይፈልገዋል። ሆኖም ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርስ የሚፈርሰው አደረጃጀቱ ላይ ትኩረት መስጠት የአሰልጣኝ ካሊድ ትኩረት የሚሰጡበት ሥራ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ካለፉት 7 ጨዋታዎች ምንም ድል ያላሳካው እንዲሁም 4 አቻ እና 3 ሽንፈት ያስተናገደው ሀዋሳ ቀስ በቀስ ከዋንጫ ፉክክሩ እየራቀ መጥቷል። 36% ብቻ የማሸነፍ ንጻሬ ያለው ቡድኑ ወደ ድል ለመመለስ ግብ ካስቆጠረ በኋላ የሚያሳየውን መዘናጋት መቀነስ ይኖርበታል። በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ቀድሞ ግብ ቢያስቆጥርም በመድን ሲሸነፍ ከሸገር አቻ ተለያይቷል። ይህም የቡድኑን በመጨረሻ ደቂቃዎች ትኩረት ማጣት የሚጠቁም ነው።

ክለቦቹ የተሰረዘውን የ2012 ውድድር ዘመን ሳይጨምር በሊጉ 13 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ሀዋሳ 4 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና 2 አሸንፏል። በቀሪ 7 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሀዋሳ ከተማ 18፣ ሀዲያ ሆሳዕና 15 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

12፡00 | ኢትዮጵያ ቡና ከ መቻል

ከመጨረሻ 6 ጨዋታዎች ሸገር ደርቢን ብቻ አሸንፈው በአራቱ አቻ ተለያይተው በአንዱ የተሸነፉት ቡናማዎቹ በ42 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። 33 ግቦች አስቆጥሮ 33 ግቦች የተቆጠሩበት ቡድኑ ከንግድ ባንክ ፣ ወልዋሎ እና አርባምንጭ ቀጥሎ ብዙ ጎሎች የተቆጠሩበት ቡድን ሆኗል። ወደ ደረጃው አናት እየገሰገሰ የነበረው ቡድኑም በተከታታይ ነጥብ መጣሎች ጉዞው ተገቷል። ሆኖም በቀሪ ጨዋታዎች በራስ መተማመኑን ጨምሮ ደረጃ ውስጥ ገብቶ ለመጨረስ ጠንካራ ተፋላሚ ሆኖ መዝለቅ ይኖርበታል።

የመሪው ሲዳማ መሸነፍን ተከትሎ ልዩነት በ7 ነጥቦች የዘለቀላቸው መቻሎች ይህንን ወርቃማ ዕድል ተጠቅመው ጫና ለመፍጠር በዛሬው ጨዋታ ማሸነፍ ብቸኛ አማራጫቸው ነው። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (37) ቀጥሎ ከፍተኛውን የግብ መጠን (36) ያስቆጠረው መቻል የዛሬ ተጋጣሚው ቡናም 33 ግቦችን ያስቆጠረ መሆኑ በሁለቱም ሳጥን ጠንካራ ተፋላሚ ሆኖ እንዲቀርብ የሚያስገድድ ነው።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል ኦካይ ጁል በቅጣት ምክንያት የማይሰለፍ ሲሆን መቻሎች ቻላቸው መንበሩ እና ውብሸት ጭላሎን በጉዳት መሐመድ አበራን በሕመም ምክንያት ሲያጣ ዓለምብርሃን ይግዛው እና ብሩክ ማርቆስ ቅጣታቸውን ጨርሰው ለጨዋታው ዝግጁ ሆነዋል።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 37 ጨዋታዎችን አድርገው ኢትዮጵያ ቡና 20 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መቻል 7 ጊዜ ድል አድርጎ በ10 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ቡናማዎቹ 56 ጦሩ ደግሞ 34 ግቦችን አስቆጥረዋል።