መቐለ 70 እንደርታዎች በቦና ዓሊ ብቸኛ ግብ ሸገር ከተማን እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊሶች በብሩክ ዓለማየሁ ብቸኛ ግብ ሀዋሳ ከተማን በተመሳሳይ 1ለ0 ውጤት አሸንፈዋል።

ሸገር ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ
በደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ የሚገኘውን ሸገር ከተማን ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ከሚታገለው መቐለ ሰባ እንደርታ ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ረገድ ተመጣጣኝ ነበር። ሆኖም ሁለቱም ቡድኖች ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ተጭኖ በመጫወትና ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ደካማ በመሆናቸው ጨዋታው በመካከለኛው ክፍል ላይ አዘንብሏል። በአጋማሹ ጭማሪ ደቂቃ (45+3) ላይ የመቐለው ደስታ ዮሐንስ ከሳጥን ጠርዝ ላይ ያገኘውን የቅጣት ምት መቶ ለጥቂት በግቡ አግዳሚ ላይ የወጣበት አስቆጪ ሙከራ ቢደረግም ሌላ ተጠቃሽ ዕድል ሳይፈጠር አጋማሹ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ ራሳቸውን አሻሽለው ወደ ሜዳ የተመለሱት መቐለ ሰባ እንደርታዎች በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመድረስ ረገድ ሙሉ ብልጫውን ወስደው ተጫውተዋል። በዚህም በ76ኛው ደቂቃ ላይ ኬኔዲ ገብረጻድቅ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መትቶት ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ ባወጣበት እንዲሁም በ82ኛው ደቂቃ ላይ ቦና ዓሊ ከሳጥን ውጭ መቶት ለጥቂት ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረው የቅጣት ምት ተጠቃሽና እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ።
ይሁንና የመደበኛው የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ (90+1) ላይ ምዓም አናብስት የልፋታቸውን ፍሬ አግኝተዋል። ከማዕዘን ተሻምቶ በግንባር የተገጨውን ኳስ ቦና ዓሊ ከሳጥን ውጭ ሆኖ በድንቅ አጨራረስ ጠቅልሎ ኳስን መረብ ላይ በማሳረፍ ክለቡ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ለሚያደርገው ትንቅንቅ እጅግ ወሳኝና ጣፋጭ የሆነች የ3 ነጥብ ድል አስመዝግቧል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሀዋሳ ከተማ
የመጀመሪያውን ግብ ለመመልከት 8 ደቂቃዎችን ብቻ በፈጀበት በዚህ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከመጀመሪያው የፊሽካ ድምፅ ጀምሮ በባላጋራቸው ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠርና ስህተቶችን በመፈለግ ፍጹም ብልጫ መውሰድ ችለዋል። በዚህም በ8ኛው ደቂቃ ላይ በስተቀኝ መስመር በኩል በተገነባ ድንቅ የኳስ ቅብብል ሀብታሙ ጉልላት አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ወጣቱ ብሩክ ዓለማየሁ በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ ፈረሰኞቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላም ማጥቃታቸውን የቀጠሉት ፈረሰኞቹ በ33ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር ፍጹም ጥላሁን በስተቀኝ በኩል የሳጥን ጠርዝ ላይ በግራ እግሩ አክርሮ የመታውን አደገኛ ኳስ ግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ አድኖበታል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት የቅዱስ ጊዮርጊስን የ 1ለ0 መሪነት ይዞ ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ሁለተኛው አጋማሽም የቅዱስ ጊዮርጊስን ብልጫ ባስመለከተ መልኩ ቢቀጥልም ረዘም ያሉ ደቂቃዎች ግን የጠራ የግብ ዕድል አልተመለከትንም። በ85ኛው ደቂቃ ላይ ፍጹም ጥላሁን መሪነታቸውን የሚያሰፋበትን አስቆጪ ሙከራ ቢያደርግም የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ሰይድ ሀብታሙ በድንቅ ብቃት አድኖበታል በመጨረሻው ክፍለ ጊዜ ሀዋሳዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጭነው ለመጫወት ቢጥሩም ጠንካራውን የፈረሰኞቹን የተከላካይ ክፍል መስበር ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ የ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

