ኢትዮጵያ ቡና ከመመራት ተነስቶ ፋሲል ከነማን 2ለ1 ሲረታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ድሬዳዋ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ፋሲል ከነማ
ቡናማዎቹን ከዐፄዎቹ ያገናኘው ቀዳሚው ጨዋታ በፈጣን ሽግግር ተጀምሮ ገና በስድስተኛው ደቂቃ ግብ አስመልክቶናል፤ የኦካይ ጁል ስህተት መነሻ የተገኘው ኳስ ተጨራርፎ ግራ መስመር ላይ ወደ ነበረው ኪሩቤል ዳኜ ጋር ደርሶ እየገፋ ሳጥን ውስጥ በመግባት መረብ ላይ አሳርፎ ዐፄዎችን መሪ አድርጓቸዋል።
አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ቡናማዎቹ ኳስ ይዘው በመጫዎት ወደፊት ለመግባት ይጣሩ እንጂ የጠራ ሙከራ አላደረጉም፤ ሆኖም ግን የአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ ይታገሱ ታሪኩ ያሻገረለትን ኳስ ሀብታሙ አሸናፊ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው አስቆጪው አጋጣሚ አቻ ሆነው ወደ መልበሻ እንዲገቡ ሊያደርጋቸው የቀረበ ሙከራ ሆኖ አጋማሹ ተገባዷል።

ጠንከር ብለው የተመለሱት ቡናማዎቹ ሳጥን ውስጥ ሲደርሱ ሀብታሙ አሸናፊ ላይ በተሰራ ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው 51ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር አዳሙ ወደግብነት ቀይሮ አቻ አድርጓቸዋል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ዐፄዎቹ ዳግም መሪ ለመሆን የቀረቡበትን ሙከራ በቃልኪዳን ዘላለም አማካኝነት አድርገው ግብ ጠባቂው ኢብራሂም ዳንላንድ እንዴትም አግዶባቸው፤ 71ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር አዳሙ የቆመ ኳስ አሻምቶ ተጨራርፎ ሀብታሙ አሸናፊ ወደ ግብ ሲመታው ተከላካዮች ለመራቅ ጥረት ሲያደርጉ ኳሱ ብዙም ሳይርቅ እዛው እራሱ አግኝቶ አስቆጥሮ ቡናማዎቹን መሪ እንዲሆኑ ካደረገ በኋላ ዐፄዎቹ ቢያንስ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት እስከመጨረሻው ቢታገሉም ግብ ማግኘት ሳይችሉ ጨዋታው ተጠናቋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ድሬዳዋ ከተማ
ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከድሬዳዋ ከተማ ያገናኘውና በጥሩ ፉክክር ጅማሮውን ያደረገው ሁለተኛው ጨዋታ በበፍቃዱ አስረሳኸኝ ከሳጥን ውጪ በተደረገ ጠንካራ ሙከራ ኢትዮ ኤሌክትሪኮችን ቀዳሚ ለማድረግ ቀርቦ ነበር። ጨዋታው ቀጥሎ በ16ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። በአንድ ለአንድ ቅብብል ኳስ ያገኘው በዛብህ መለዮ ያሾለከለትን ኳስ ፓትሪክ ሲቦማና በመሃል ሾልኮ በመውጣት ኳስና መረብን አገናኝቶ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ቀዳሚ አድርጓቸዋል።
የአቻነት ግብ ፍለጋ ወደ ፊት መሄድ የጀመሩት ብርቱካናማዎቹ፥ በተደጋጋሚ በሦስተኛው ሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ በሚቆራረጡ ኳሶች አደጋ መፍጠር ሳይችሉ ሲቀሩ አስተውለናል። በአጋማሹም ያሬድ ታደሰ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ መትቶ ለጥቂት ከፍ ብሎ በግቡ አግዳሚ አናት ላይ ያለፈበት ሙከራ የሚጠቀስ ቢሆንም፥ ጥረታቸው የጠራ ሙከራ ሳያስመለክተን ለእረፍት አቅንተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ተጠናክረው የተመለሱት ብርቱካናማዎቹ፥ የአቻነት ግብ አጋማሹ እንደጀመረ አግኝተዋል። በሳጥን ውስጥ የተጣለውን ኳስ መሐመድኑር ናስር ተቆጣጥሮ ለመምታት ሲዘጋጅ ተከላካዩ ኢስማኤል ናሂማና በሠራው ጥፋት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት አስቻለው ታመነ አስቆጥሮ አቻ አድርጓቸዋል።
የአቻነት ግብ ካገኙ በኋላም የተነቃቁት ብርቱካናማዎቹ የጨዋታ ብልጫ ወስደው ተጋጣሚዎቻቸውን የፈተኑ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በተለይም በሁለት አጋጣሚዎች አቤል ነጋሽ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ በመምታት ያደረጋቸው ሙከራዎች ለጥቂት ከፍ ብለው ባያልፉ ኖሮ መሪ መሆን የሚችሉበት ሰፊ አጋጣሚ ነበር።
በቀዝቃዛ እንቅስቃሴ የተመለሱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ሲገቡ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሆነው መቀጠል ተስኗቸው ቆይተዋል። በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ቤዛ መድህን ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ አብነት ተስፋዬ ብቻውን ሆኖ አግኝቶት ያመከነው አጋጣሚ የጨዋታውን ውጤት መቀየር የሚችል ቢሆንም፥ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ጨዋታው ነጥብ በማጋራት ተጠናቋል።

