የቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ33ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

የቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ33ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 33ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በሚደረጉ ሶስት ጨዋታዎች ፍፃሜውን ሲያገኝ፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።

አዳማ ከተማ ከ ወልዋሎ ዓዲግራት

በደረጃ ሰንጠረዡ የታችኛው ክፍል ላይ አንጻራዊ መረጋጋትን ለመፍጠር የሚፋለሙት አዳማ ከተማ እና ወልዋሎ ዓዲግራት በ33ኛ ሳምንት ወሳኝ ፍልሚያ ያደርጋሉ። በ38 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማ ዋነኛ ታክቲካዊ ጥንካሬው የመስመር ተጫዋቾቹን ፍጥነት በመጠቀም ወደ ሳጥን በተደጋጋሚ መድረስ መቻሉ ቢሆንም ማጥቃትን መሠረት አድርጎ ወደ ፊት በሚሳብበት ወቅት በፈጣን መልሶ ማጥቃት የኋላ ክፍሉ በቀላሉ ለቁጥር ብልጫ መጋለጡ ትልቅ ድክመቱ ነው። ባለፈው ሳምንት በፋሲል ከነማ 3 ለ 1 የተሸነፈበት መንገድ ይህንን ክፍተት ያሳየ በመሆኑ ዛሬ ይህንን አርሞ ወደ ድል ለመመለስ መጫወት ይኖርበታል።

በተቃራኒው በ39 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ወልዋሎ ዓዲግራት የራሱን ሳጥን በአግባቡ በመቆለፍ የተጋጣሚን ጫና ማክሸፍ እና ፈጣን ሽግግሮችን መጠቀም መቻሉ ትልቁ ስልታዊ ጥንካሬው ነው። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ካሳየው ጥሩ መነቃቃት ጀርባ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክን 2 ለ 1 ያሸነፈበት ታክቲክ የቡድኑን የማሸነፍ ወኔ ይመሰክራል። ይሁን እንጂ ተከላካዮቹ ሳጥናቸው ዙሪያ ጥቅጥቅ ብለው በሚቆሙበት ወቅት ከሳጥን ውጪ ለሚመቱ የርቀት ኳሶች የሚሰጡት ምላሽ የትኩረት ማጣት የሚታይበት መሆኑ የቢጫ ለባሾቹ ዋነኛ ድክመት ነው። አዳማ የመስመር ጥቃቱን ተጠቅሞ የወልዋሎን የተከላካይ ግንብ ለመስበር በሚያደርገው ጥረት እና ወልዋሎዎች ስህተትን ጠብቀው በሚያደርጉት ፈጣን ሽግግር መካከል የሚታየው ፍልሚያ ጨዋታውን ተጠባቂ ያደርገዋል።

በ2012 የተሰረዘውን የውድድር ዘመን ሳይጨምር ሁለቱ ቡድኖች 7 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ 3 ሲያሸንፍ፣ ወልዋሎ አንድ አሸንፎ ሶስቱን ጨዋታዎች አቻ ተለያይለዋል። አዳማ 10፣ ወልዋሎ 4 አስቆጥረዋል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

አርባምንጭ ከተማ በ29 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 20ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የህልውና ትግል እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንዱን ብቻ ነው (ሁለቱን ተሸንፎ በሁለቱ አቻ ተለያይቷል)። የቡድኑ መልካም ጎን ከትልልቅ ቡድኖች ጋር እልህ አስጨራሽ ፉክክር የመግጠም ወኔው ቢሆንም የፊት መስመሩ ግብ የማስቆጠር ድክመት እና ጨዋታዎችን መርታት አለመቻሉ እንደ ዋና ደካማ ጎን ይጠቀሳል። አዞዎቹ የዛሬውን ጨዋታ አሸንፈው ከወራጅ ቀጠናው አዙሪት ለመውጣትና በሊጉ የመቆየት ተስፋቸውን ለማለምለም በዋናነት የተከላካይ ክፍሉን ማጠንከር እና የፊት መስመሩ ላይ የሚታየውን የመግባባት ስህተት ማስተካከል ይኖርባቸዋል ይህንን ማድረግ ከቻሉ ግን ከሊጉ መሪ ነጥቀው የሶስት ነጥብ ባለቤት የመሆን ሰፊ ዕድል ይኖራቸዋል።

ሲዳማ ቡና በአንጻሩ በ55 ነጥብ የሊጉን መሪነት በቁጥጥሩ ስር ቢያደርግም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በተከታታይ ያስተናገዳቸው ሦስት ሽንፈቶች በዋንጫ ጉዞው ላይ ፈታኝ ጥላ አጥልተውበታል። የቡድኑ ትልቁ ጥንካሬ በውድድር ዓመቱ በሙሉ ያስመዘገበው ወጥ አቋምና የሊጉን የፊት መስመር የሚመራው የአጥቂ ክፍሉ ቢሆንም በቅርብ ሳምንታት የተከላካይ ክፍሉ መላላትና ወሳኝ ነጥቦችን በቀላሉ አሳልፎ መስጠቱ እንደ ደካማ ጎን እየታየበት ይገኛል። ዛሬ በሚደረገው ወሳኝ ፍልሚያ የቡድኑ ዋነኛ ትኩረት ይህንን የቅርብ ጊዜ የውጤት መውረድ በአስቸኳይ በመግታት በሁለት ነጥብ ልዩነት ብቻ ተከታትሎት ከሚገኘው መቻል ስጋት ራሱን ማራቅና ወደ ቀደመው የማሸነፍ ግርማው ተመልሶ የክብር ዘውዱን ለመጨበጥ ቆርጦ መነሳት ላይ ነው።

በአርባምንጭ ከተማ በኩል ሁሉም የቡድን አባላቶች ለዛሬው ወሳኝ ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። ሲዳማ ቡና ተመስገን በጅሮንድ እና መኳንንት ካሳን በጉዳት ለዛሬው ጨዋታ አያሳለፍም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ20 ጊዜያት ተገናኝተው 14 ጨዋታዎች አቻ ሲጠናቀቁ አርባምንጭ ከተማ 4 ሲዳማ ቡና ደግሞ 2 ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችለዋል።

ነገሌ አርሲ ከ ምድረገነት ሽረ

ነገሌ አርሲ በ51 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የላቀ ግስጋሴ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ፣ በሁለቱ አቻ ተለያይቶ በአንዱ ተሸንፏል። የቡድኑ መልካም ጎን ፈጣን የሆኑ የመስመር አጥቂዎቹ  እንዲሁም ጠንካራ የመከላከል ክፍሉ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት በመቻል 4 ለ 0 መረታቱ የኋላ ክፍሉ መላላቱን ያሳየ ደካማ ጎኑ ነው። ነገሌ አርሲ 3 ነጥቡን ይዞ ለመውጣት ባለፈው ሳምንት የተበላሸውን የተከላካይ ክፍል በፍጥነት ማስተካከልና የመሃል ሜዳ የበላይነቱን ቀድሞ መቆጣጠር ይኖርበታል ይህንን ካደረገ ጨዋታውን የማሸነፍ ሰፊ ዕድል አለው።

በአንጻሩ በ36 ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ብርቱ ትግል እያደረገ የሚገኘው ምድረገነት ሽረ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ቀንቶት በአንዱ አቻ ተለያይቶ በሁለቱ ደግሞ ሽንፈት አስተናግዷል። ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ቡናን 1 ለ 0 ያሸነፈበት የጨዋታ ስልት ትልቅ መነሳሳትን የፈጠረ ቢሆንም የፊት መስመር ያለበቶ የግብ ማስቆጠር ችግር ደካማ ጎኑ ነው። ሽረዎች የዛሬውን ጨዋታ አሸንፈው ከስጋት ለመራቅ የነገሌ አርሲን ፈጣን ማጥቃት መግታትና ባለፈው ሳምንት ያገኙትን የማሸነፍ ስነ-ልቦና ተጠቅመው ስህተቶችን በአግባቡ መጠቀም መቻል አለባቸው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አንድ ጊዜ ብቻ የተገናኙ ሲሆን ይህንንም ጨዋታ ነገሌ አርሲ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።