ታላቁ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የስያሜ ስፖንሰር ስምምነት ፈፀመ

ታላቁ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የስያሜ ስፖንሰር ስምምነት ፈፀመ


👉 “የሀገር ዋልታ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመሰል ማሕበራዊ ሃላፊነት ላይ መሳተፉ ትልቅ ደስታ እና ኩራት ይሰማዋል”

👉 “የትኬት ሽያጩ በሲቢኢ ብር ብቻ ይፈፀማል”

👉 “ቢያንስ 250 ጨዋታዎች የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ይሰጣቸዋል”

👉 “የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባይኖር የቀጥታ ስርጭቱ እውን ለማድረግ ከባድ ነበር”

በኢትዮጵያ ስፖርት እድገት ትልቅ አስተዋፅዖ በማድረግ የሚታወቀው እና በ2018 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የስያሜ ስፖንሰርሺፕ በመግዛት የፕሪምየር ሊጉ አጋር የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዛሬው ዕለት የ2019 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዓመት የስያሜ ስፖንሰር ለመግዛት ስምምነት ፈፅሟል።

በፌርማ ስነ ስርዓቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አክቲንግ ፕሬዚደንት አቶ ደረጄ ፉፋ፣ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክስዮን ማሕበር የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ብርጋዴር ጀነራል ኑሩ ሙዘይን፣ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክስዮን ማሕበር ስራ አስከያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ፣ የኦቢኤን ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍሰሐ በላይነህ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የበላይ አመራር እና የባንኩ ቤተስብ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች እና ደጋፊዎች በተገኙበት መድረክ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አክቲንግ ፕሬዚደንት አቶ ደረጄ ፉፋ ባንካቸው የስፖርቱ ቤተሰቡ ሊጉን በቤቱ ሆኖ እንዲከታተል ጉልህ አስተዋፅዖ እንዳደረገ ገልፀው የሀገር ዋልታ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመሰል ማሕበራዊ ሃላፊነት ላይ መሳተፉ ትልቅ ደስታ እና ኩራት እንደሚሰማው በአፅንኦት ገልፀዋል። በተጨማሪም ስፖርት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው በመጥቀስ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርቱን ለመደገፍ የወሰደው ትልቅ ሃላፊነት ሌሎች መንግስታዊ እና የግል ተቋማት እንዲከተሉት ጥያቄ አቅርበዋል።

በመቀጠል ሃሳባቸውን የሰጡት የኦቢኤን ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍሰሐ በላይነህ የባለፈው ዓመት ብዙ ስኬት የተመዘገበበት እንደነበር ገልፀው የቴሌቪዥን ጣብያው ሊጉ ከአራት ስታድየሞች የቀጥታ ሽፋን እንደሰጠ እንዲሁም በተመሳሳይ ሰዓት የተካሄዱትን ጨዋታዎች በሦስት የአገር ውስጥ ቋንቋዎች በነፃ እንዳስተላለፈ በመጥቀስ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባይኖር የቀጥታ ስርጭቱ እውን ለማድረግ ከባድ እንደነበር ተናግረዋል። ስራ አስፈፃሚው በተጨማሪም ቢያንስ 250 ጨዋታዎች የቀጥታ ስርጭቱ ሽፋን እንደሚሰጣቸው እና ስርጭቱ ከባለፈው ዓመት በተሻለ ጥራት ለሚልዮኖች በነፃ እንደሚያስተላልፉ ተናግረዋል።

ቀጥለው መድረኩን የተረከቡት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክስዮን ማሕበር ስራ አስከያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ከ83 ዓመት ዕድሜ ያለው አንጋፋ ተቋም እና 7 ዓመት ዕድሜ ያለው የቴሌቪዥን ጣብያ ጋር አብረው መስራታቸው ደስታ እንደሚሰማቸው በመግለፅ አክስዮን ማሕበሩ ያለፉትን ዓመታት በአጠቃላይ 1.2 ቢልዮን ብር ለክለቦች እንዳከፋፈለ እና ከስታድየም ገቢ ምንም አይነት ክፍያ እንደማይወስድ አንስተዋል።