ያለፉትን አስራ ሁለት ዓመታት ከአስራ ሁለት ለባሾቹ ጋር አብሮ የዘለቀው ሐበሻ ቢራ ከፍተኛ የሆነ የስፖንሰር ስምምነት ፈፅሟል

ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል በተካሄደውና የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ሀበሻ ቢራ ዳግም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በአጋርነት በመዝለቅ ለተጨማሪ ሦስት ዓመት አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን አዲስ የውል ስምምነት ተፈራርሟል።
የሐበሻ ቢራ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኦዎ ኦዎሃሪ 12 ቁጥር ለባሽ ደጋፊዎች ለክለባቸው ያላቸው ድጋፍ በከፍታውም በዝቅታውም ጊዜ እንደማይቋረጠው ሁሉ እኛም ከክለቡ ጎን ለመቆም ድጋፋችን የማይናወጥና በጽኑ ቁርጠኝነት ላይ የተመሰረተ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል የቦርድ አባሉ አቶ መንግስቱ ታደሰ ሲናገሩም የኢትዮጵያ ቡና እና ሐበሻ ቢራ ያላቸው ዝምድና የማይገመድ አብሮ ለዘመናት ትውልድ ተሻጋሪ ሆነው የሚቀጥል እንደሆነ ያረጋገጡ ሲሆን ይህ ከፍተኛ ስምምነት ለእኛ ደጋፊዎች የአደራ ስምምነት ነው ብለዋል።
የስምምነቱ ዋና ዋና ነጥቦች
ሐበሻ ቢራ በዓመት 45 ሚሊዮን ብር በድምሩ ለሦስት ዓመታት 135 ሚሊየን ብር የሚከፍል ይሆናል።
በተጨማሪ ለተለያዮ ወጪዎች ድጋፍ ለማድረግ በየዓመቱ 13 ሚሊየን ብር የሚሰጥ ይሆናል። በአጠቃላይ ሐበሻ ቢራ በሦስት ዓመት ውስጥ ከ160 ሚሊየን ብር በላይ የስፖንሰር ስምምነት እንደተፈፀመ ለማወቅ ተችሏል።
– በተለየ ሁኔታ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና የ2019 የውድድር ዘመንን አሸናፊ ሆኖ የሚያጠናቅቅ ከሆነ 15 ሚሊየን ብር ለመክፈል ተስማምቷል
– ከዋናው ስምምነት በተጨማሪ ከእያንዳንዱ የቢራ እና ድራፍት ገቢ ለክለቡ የሚሰጥ ይሆናል።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል ሐበሻ ቢራን ክለቡ በዋናው ቡድን እና የሴቶቹ ቡድን በማልያ ላይ ያስተዋውቃል ፣ ኢትዮጵያ ቡና በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ የሀበሻን ሎጎ ማስተዋወቅ እና በተጨማሪም በሚያዘጋጃቸው የተለያዩ ፕሮግራሞች፣ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ሐበሻ ቢራን የማስተዋወቅ ሥራ የሚሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።

