ወደ “Home And Away” ፎርማት በተመለሰው ሊጋችን በመጀመሪያው ሳምንት በሜዳቸው ከተጫወቱ ዘጠኝ ቡድኖች አንዳቸውም ድል አለማድረጋቸው የሳምንቱ የመጨረሻ ዐበይት ጉዳያችን ሆኗል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዕለተ ዓርብ መጋቢት 4/2012 ዓ/ም የኮቪድ ወረርሺኝ ወደ ሀገራችን ከገባበት ዕለት ጀምሮ በ “Home And Away” ፎርማት መካሄዱን አቁሞ ነበር። ሆኖም ላለፉት 6 ዓመታት ( 5 ዓመታት በሱፐር ስፖርት ፣ አንድ ዓመት በ OBN ) የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን እየተሰጣቸው ጨዋታዎች በተመረጠ ሜዳ መደረጋቸውን ቢቀጥሉም ስክሪን ላይ የሚታዩ ባዶ የደጋፊ መቀመጫወች የሊጉን ሳቢነት ከመቀነስም ባሻገር የተለያዩ አምራቾች በማስታወቂያዎች ሊጉን እና ክለቦቹን በገንዘብ እንዳያግዙ ማነቆ ሆኖባቸው ከርሟል።
በ2019 የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከስድስት ዓመታት በፊት እንደነበረው ክለቦች በሚያስመዘገቡት ሜዳ ወደ መጫወት መጥተው አሁን ላይ በሰባት ስታዲየሞች ውድድሩ ለአንድ ሳምንት ተደርጎ ነገ ሁለተኛው ሳምንት ይጀምራል።
በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ከተደረጉ ዘጠኝ ጨዋታዎች ሦስቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ስድስቱ ጨዋታዎች ባለሜዳዎቹ የተሸነፉበት ሳምንት ነበር። ይባስ ብሎም ከዘጠኙ ባለሜዳዎች ሁለቱ ብቻ ግብ ማስቆጠር ችለዋል።
እኛም ትኩረታችንን የሳበውን ነገር ልናጋራችሁ ወደድን !
ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፊት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ”Home & Away” ፎርማት በየክልሉ በሚገኙ ሜዳዎች ሲካሄድ የነበረበት ወቅት ለባለሜዳ ቡድኖች ከፍተኛ ጥቅም ይሰጥ ነበር። ለዚህም ምክንያት ተብለው በብዙዎቹ የሚታመኑት ዳኞች በደጋፊዎች በተሞላ ስታዲየም ውስጥ ጨዋታዎችን ሲመሩ በደጋፊዎች ጩኸት ፣ ተቃውሞ እና ጫና ምክንያት ለባለሜዳው ያደላ ውሳኔ ሲወስኑ ይስተዋሉ ነበር። ሌላው ደግሞ የቪዲዮ ሽፋን በሌለበት ሁኔታ ዳኞች የሚሠሯቸውን ስህተቶች ወይም የሚወስኗቸው አወዛጋቢ ውሳኔዎችን በድጋሚ በቪዲዮ ዐይቶ ማረጋገጥ አለመቻል ዳኞች ከተለያዩ የተጋጣሚ ቡድን ደጋፊዎች እና የክለቡ አባላት የሚመጡባቸውን ጥያቄዎች እንደማምለጫ ይጠቀሙባቸው ነበር።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት የተለያዩ ሜዳዎች ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎችን በተመሳሳይ ሰዓት የቀጥታ ሥርጭት እየሰጠ የሚገኘው ሀገር በቀሉ የብሮድካስት ተቋም ኦቢኤን ግን በርካታ ጥቅሞችን ይዞ መጥቷል። ከእነዛም መካከል ዳኞች ከሜዳ ውጪ ላሉ ባለሙያዎች እና እጅግ በርካታ ደጋፊዎች እንዲሁም የሙያ አጋሮቻቸው ሲሉ የደጋፊዎችን ጩኸት ፈርተው ያልፈለጉትን ውሳኔ ለመስጠት ከመገደድ ይልቅ ሕጉን ብቻ ተከትለው እንዲዳኙ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። እንዲሁም ሜዳ ውስጥ የሚገኙ ደጋፊዎች እና የክለብ አመራሮች በሚፈጥሯቸው አላስፈላጊ ሰጣ እገባዎች እና የጨዋታ ዳኞች ላይ የሚወረውሯቸው ስድቦች በአወዳዳሪው አካል ተገቢውን ቅጣት ማግኘታቸው ፣ ለዳኞች ደግሞ በሚሰጧቸው እያንዳንዱ ውሳኔዎች ውስጥ የሙያ ስማቸውን እንዲጠብቁ መገደዳቸው እንደ ጠንካራ ጎን ይነሳሉ።
ከረጅም ጊዜያት በኋላ በሜዳቸው የሚጫወቱ ቡድኖች “በደጋፊያችን ፊት የግዴታ ማሸነፍ አለብን” በሚል ከባድ የስነልቦና ጫና ተረጋግተው ለመጫወት መቸገር እና ከታቀደው አቀራረብ መውጣት እንዲሁም ከሜዳቸው ውጪ ሄደው የሚጫወቱ ቡድኖች ምንም ዓይነት ጫና ስለሌለባቸው በተረጋጋ አጨዋወት የተመሰረተ የታክቲክ የበላይነት ሦስት ነጥብ ያገኙበትን ድል ሊቀዳጁ ችለዋል።
የአንድ ሳምንት ብቻ ጨዋታ ብዙ ፍርዶችን ለመስጠት በቂ ባይሆንም ቀደም ሲል የነበረው “ባለሜዳ አይሸነፍም” የሚለው አስተሳሰብ እንዲቀር ትልቅ አስተዋጽኦ ካላቸው ምክንያቶችን ውስጥ በዋናነት ከላይ እንደጠቀስነው የቀጥታ ሥርጭት በመኖሩ፣ የዳኞች ተጠያቂነት በመጨመሩ እና ዳኞች ከደጋፊ ጫና ነፃ የመሆን ዕድል በማግኘታቸው ነው የሚል አመክንዮ ማንሳት ይቻላል። ይህም ውድድሩ ይበልጥ ፍትሐዊ እና በሜዳ ላይ ባለው የቡድኖች የታክቲክ የበላይነት ብቻ የሚወሰን እንዲሆን መንገድ ከፍቷል።

