ወጣቱ ሔኖክ ዛሬም ለንግድ ባንክ ድል አስገኝቷል

ወጣቱ ሔኖክ ዛሬም ለንግድ ባንክ ድል አስገኝቷል

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዛሬ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቻልን በማሸነፍ ሙሉ ሦስት ነጥብ ሲያገኝ ወላይታ ዲቻ በበኩሉ በጭማሪ ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ ከሽንፈት ተርፎ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ተጋርቷል።

በአብዩ አረጋሽ

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1–0 መቻል

በአዲስ አበባ ስታድየም በተደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ47ኛው ደቂቃ ሄኖክ ኤርምያስ ባስቆጠረው ግብ መቻልን 1ለ0 ማሸነፍ ችሏል።

በጥብቅ ፉክክር የታጀበው ጨዋታ እስከ በውጥረቶች የተሞላ ሆኖ የተከናወነ ሲሆን የወጣቱ አጥቂ ሄኖክ ኤርምያስ ግብ ለንግድ ባንክ የድል ቁልፍ ሆኗል። በዚህም ክለቡ ሦስት ነጥቦችን በማሳካት በሊጉ ያለውን የውድድር ጉዞ በድል ቀጥሏል።

ሀድያ ሆሳዕና 1–1 ወላይታ ዲቻ

በሌላኛው ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕና እና ወላይታ ዲቻ በአብዮ ኤርሳሞ ስታዲየም ባደረጉት ፍልሚያ 1ለ1 በሆነ ውጤት ተለያይተዋል።

ጨዋታው ያለ ግብ ይጠናቀቃል ተብሎ በተጠበቀበት ወቅት ሀድያ ሆሳዕና በ87ኛው ደቂቃ ፕሪንስ ባዱ ባስቆጠረው ግብ መሪነቱን ይዞ ነበር። ይህ ግብ ለሀድያ የድል ተስፋን ያጫረ ቢሆንም ወላይታ ዲቻ እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ትግሉን አላቋረጠም ነበር።

በ90+4ኛው ደቂቃ መሳይ ሰለሞን ለወላይታ ዲቻ ወሳኝ የአቻነት ግብ በማስቆጠር ቡድኑን ከሽንፈት አድኗል። በመጨረሻው ቅጽበት የተቆጠረችው ግብ ሀድያ ሆሳዕናን የድል እድል ያሳጣች ሲሆን ለወላይታ ዲቻ ግን የማታ ማታ አንድ ነጥብ አስገኝታለች።

በዚህም ሁለቱ ክለቦች አንድ አንድ ነጥብ ተጋርተው ጨዋታቸውን ሲያጠናቅቁ የወላይታ ዲቻ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ከጨዋታዎቹ ትኩረት የሳበ ክስተት ሆኗል።