የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የፎርማት ለወጥ ተደረገበት

ከፍተኛ ሊጉ በ36 ክለቦች መካከል በሦስት ምድቦች ተከፍሎ እንደሚካሄድ ተረጋግጧል።

የሀገሪቱ የሁለተኛ ዕርከን ውድድር የሆነው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2010 የውድድር ዓመት ግምገማ እና የ2011 ዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓት ዙሪያ በኢትዮጵያ ሆቴል እየተካሄደ የሚገኘው ስብስባ ለውድድሩ አዲስ አካሄድን አምጥቷል። የፌዴሬሽኑ ም/ፕሬዘዳንት ኮነሬል ዐወል አብዱራሂም በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ የዘንድሮው የሊጉ ውድድር በተለየ መንገድ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

በዚህም መሰረት የተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ከ32 ወደ 36 ከፍ እንዲል ሲደረግ የምድቦቹ ስያሜም ከ ‘ሀ’ እና ‘ለ’ ወደ ማዕከላዊ ምድብ ፣ መካከለኛ እና ደቡብ ምስራቅ ምድብ እና መካከለኛ እና ደቡብ ምዕራብ ምድብ ተቀይሯል። በም/ፕሬዘዳንቱ ማብራሪያ መሰረት በሊጉ የተካተቱት ተጨማሪ አራት ክለቦች በአምናው ውድድር ከወረዱት ውስጥ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ እንደሚሆኑም ተገልጿል። በመሆኑም ከምድብ ሀ ፌደራል ፖሊስ እና ወሎ ኮምቦልቻ ከምድብ ለ ደግሞ ሻሸመኔ ከተማ እና ድሬዳዋ ፖሊስ በሊጉ መወዳደራቸውን ይቀጥላሉ።

በውድድሩ በቀጣይነት ከአራት ክልሎች እና ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡት 36 ክለቦች በሦስት ምድቦች ተከፍለው የሚወዳደሩ ይሆናል። በተደረገው ለውጥ በዋናነት የክለቦች ጂኦግራፊያዊ መቀመጫ ከግምት ውስጥ የገባ ሲሆን ዓመታዊ የጉዞ ወጪያቸውን ለመቀነስም ጥረት እንደተደረገ ተጠቁሟል። በመሆኑም ክለቦች ቀድሞ የሚያደርጉት የጨዋታ ቁጥር ከ30 ወደ 22 የሚቀንስ በመሆኑ ውድድሩ በቶሎ እንዲጠናቀቅ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ተነግሯል። ከዚህም ባለፈም አዲሱ ፎርማት ጨዋታዎች በሁለቱ የዕረፍት ቀናት እንዲካሄዱ የሚረዳ መሆኑም ተጨማሪ ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጓል።

በጉዳዩ ዙሪያ ሁሉም ተሳታፊ ክለቦች የተሰማሙ ሲሆን ናሽናል ሲሚንት እና አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ በተመደቡባቸው ምድቦች ላይ ከርቀት አንፃር ጥያቄ ማንሳታቸውን ተከትሎ ማስተካከያዎች ተደርገው በሦስቱ ምድቦች የሚካተቱት ክለቦች ከዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓቱ በፊት ያፋ እንደሚደረጉ ይጠበቃል።


ማስታወቂያ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የዋናው እግርኳስ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የቪድዮ ቀረጻ እና የጨዋታ ትንተና የሚያደርግ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አካላት በስራው ላይ ያላቸውን የታደሰ ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ ሜክሲኮ በሚገኘው የክለቡ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ የፍላጎት ማሳወቂያ እና የመወዳደርያ ሰነድ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ለተጨማሪ መረጃ – 0115-534949 ; 0115-532051

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ