ሻሸመኔ ከተማ ግብ ጠባቂ ሲያስፈርም የሁለት ተጫዋቾችን ውል አድሷል

በቢሾፍቱ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እየሰሩ የሚገኙት ሻሸመኔ ከተማዎች የቀድሞው ግብ ጠባቂያቸውን ሲያስፈርሙ የሁለት ተጫዋቾችን ኮንትራትም አራዝመዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ ረዘም ካሉ ዓመታቶች በኋላ አድጎ መሳተፍ የሚጀምረው ሻሸመኔ ከተማ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ያስፈረማቸውን አዳዲስ ተጫዋቾችን ከነባሮቹ ጋር በማጣመር በአሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ እና ረዳቶቹ መሪነት የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በቢሾፍቱ ከተማ እየሰሩ የሚገኝ ሲሆን አሁን ደግሞ ከዚህ ቀደም በክለቡ መጫወት የቻለውን ግብ ጠባቂው አቤል ማሞን ሲያስፈርም የሁለት ነባር ተጫዋቾችን ውልም ስለ ማራዘሙ ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል።

ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ የክለቡ አዲሱ ፈራሚ ሆኗል። በሻሸመኔ ከተማ ከረጅም ጊዜያት በፊት ተጫውቶ በመቀጠል በሙገር ሲሚንቶ ፣ በመቻል ፣ በኢትዮጵያ ቡና እና የተጠናቀቀውን ዓመት ደግሞ በአርባምንጭ ከተማ ቆይታን ያደረገው የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የግብ ዘብ የነበረው አቤል ዳግም ሻሸመኔን ተቀላቅሏል።

ከአዲስ ፈራሚው በተጨማሪ ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድግ አስተዋጽኦን ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል የተከላካይ አማካዩ ጌታአለም ማሙዬ እና የመስመር አጥቂው አሸናፊ ጥሩነህን ውልም ታድሷል።