የመስመር አጥቂው ከብሔራዊ ቡድን ውጭ ሆኗል

ከግብፅ አቻው ጋር ለሚደረግ ጨዋታ በዝግጅት ላይ በሚገኘው ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ውስጥ የመስመር አጥቂው ከስብስብ ውጭ መሆኑ ታውቋል።

የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ መጨረሻ ጨዋታውን ጳጉሜ 4 ከግብፅ ጋር ጨዋታውን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዝግጅቱን ከጀመረ ሦስተኛ ቀን ላይ ደርሷል። ሽመልስ በቀለ እስካሁን ብሔራዊ ቡድኑን ያልተቀላቀለ ሲሆን ምኞት ደበበ በጉዳት ምክንያት በራምኬል ጀምስ ተተክቶ ዝግጅቱን እየከወነ ይገኛል። አሁን ደግሞ የመስመር አጥቂው ቢንያም በላይ ከብሔራዊ ቡድኑ ውጭ መሆኑን አረጋግጠናል።

ቢንያም የመጀመርያው ቀን ልምምድ በግል ጉዳይ ምክንያት ያልተገኘ ቢሆንም በትናትናው ዕለት ረፋድ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሜዳ ላይ በመገኘት ከቡድኑ ጋር አብሮ መስራት ችሎ ነበር። ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም በነበረው ልምምድ አለመገኘቱን የታዘብን ሲሆን በምን ምክንያት እንደቀረ ለማወቅ ባደረግነው ጥረት ከፌዴሬሽኑ በኩል በጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ውጭ መሆኑ ተገልፆልናል።