ድሬዳዋ ከተማ ጋናዊ ተከላካይ አስፈርሟል

በአሰልጣኝ አስራት አባተ የሚመራው ድሬዳዋ ከተማ ጋናዊ የመሐል ተከላካይ ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።

ለቀጣዩ ዓመት የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው በሐሮማያ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እየሰሩ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች በአሰልጣኝ አስራት አባተ መሪነት አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን በመያዝ ልምምዳቸውን አጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን ጋናዊውን የመሐል ተከላካይ እስማኤል አብዱልጋሊዮን ዘጠነኛ የክለቡ አዲስ ፈራሚ በማድረግ ስለ ማስፈረማቸው የዝግጅት ክፍላችን ያገኘችው መረጃ አመላክቷል።

27 ዓመት ዕድሜው ላይ እንዳለ የሚነገርለት ተከላካዩ በሀገሩ ክለቦች ዋ ኦል ስታርስ ፣ ካሬላ ዩናይትድ እና አሳንቲ ኮቶኮ ከተጫወተ በኋላ በመቀጠል ለኢራቁ ክለብ አልታላባ የተጠናቀቀውን ዓመት ደግሞ በኮንጎው ክለብ ቲፒ ማዜንቤ ቆይታን አድርጓል።

ከክለቡ ጋር በገንዘብ አከፋፈል ጉዳዮች ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቶ በፊፋ ጉዳዩ እየታየለት የሚገኘው እስማኤል ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ድሬዳዋ ከተማን በይፋ ተቀላቅሏል።