የኬንያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል

ለአለም ከ20 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ ለመሳተፍ ሀገራት የአንደኛ ዙር ጨዋታቸውን በዚህ ሳምንት ያደርጋሉ፡፡ በቅድመ ማጣርያው ቦትስዋናን በቀላሉ ያሸነፈችው ኬንያም ኢትዮጵያን ትገጥማለች፡፡

በአሰልጣኝ ካሮሊን አቼንግ የሚመራው የኬንያ ብሔራዊ ቡድን 20 ተጫዋቾችን ያካተተ እና 29 አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን በመያዝ ትላንት ረፋድ ወደ ሀዋሳ በማምራት መቀመጫውን በሳውዝ ስታር ሆቴል ያደረገ ሲሆን በዛሬው እለትም ጨዋታው በሚደረግበት ስታድየም የመጨረሻ ልምምዱን 10:00 ላይ አከናውኗል፡፡ ለ1 ሰአት ያህል በቆየው ልምምድም ኳስ ከመስመር ላይ ኳስ የማሻገር ና በፍጥነት ወደ ግብ መድረስ ላይ ትኩረት ያደረገ ስራን ሰርተዋል፡፡

የኬንያ አሰልጣኝ ካሮሊን አቼንግ ስለነገው ጨዋታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡

ስለ ቡድናቸው

ቡድናችን ጥሩ ነው፡፡ ለነገው ጨዋታ በሚገባ ተዘጋጅተናል፡፡ ያለን ስሜትም ጥሩ ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ ስለተዘጋጀንና ጥሩ ሁኔታ ላይ ስለምንገኝ ነገ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖረን ጨዋታ የተሻለ እንቅስቃሴ የምናሳይበት ይሆናል፡፡

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ከባድ እንደሚሆን አስባለሁ፡፡ ሆኖም ግን የመጣነው ውጤት ለመያዝ ነው፡፡ ይህ ባይቻልም እንኳን ውጤቱን አጥብበን በመውጣት ቀጣይ ጨዋታችን በሜዳችን ስለሆነ ስህተቶቻችንን የምናርምበት ይሆናል፡፡

ስለ ቡድኑ
ሁሉም ተጫዋቾቻችን ከዛው ከኬንያ ፕሪሚየር ሊግ ነው የመረጥናቸው፡፡ በሊጉ ጥሩ የሚባሉ ታዳጊዎችን በስብስባችን ይዘናል፡፡ ሌላ በውጭ ሀገራት የሚጫወቱ ተጫዋቾች ስለሌሉን ማካተት አልቻልንም፡፡

ስለተጋጣሚያቸው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ እንደሆነ ሰምተናል፡፡ የጥሩ ተጫዋቾች ስብስብ እንዳለው እና የውስጥ ውድድራችሁም ጠንካራ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሌላ የተለየ መረጃ ባናውቅም በጨዋታ ውስጥ የተወሰነ ነገር ለማወቅ እንምክራለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *