ሪፖርት | መከላከያ ወሳኝ ድል አሳክቷል

በ20ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታ መከላከያ በፍፁም ገ/ማርያም የጭማሪ ደቂቃ ጎል አርባምንጭ ከተማን በማሸነፍ ከሁለት ጨዋታዎች በኃላ ወደ ድል ተመልሷል።

መከላከያ አዳማ ላይ ሽንፈት ሲያስተናግድ ከተጠቀመበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ከቅጣት የተመለሰው ምንተስኖት ከበደን በአብነት ይግለጡ ምትክ ቀኝ መስመር ተከላካይ ስፍራ ላይ ሲጠቀም አማካይ ክፍል ላይ አማኑኤል ተሾመን በበሀይሉ ግርማ እንዲሁም አዲስ ፈራሚው ፍፁም ገብረማርያምን በማራኪ ወርቁ ምትክ አስገብቷል። የቀኝ መስመር ተከላካያቸው ወርቅይታደል አበበን በቅጣት ያጡት አርባምንጮች ቦታውን በመስመር አጥቂው ፀጋዬ አበራ ሸፍነው አስጨናቂ ፀጋዬን በመስመር አጥቂነት ተጠቅመዋል። አሰልጣኝ እዮብ ማለ ከኢትዮጵያ ቡናው ድል የቀየሩት ሌላኛው ተጨዋች በረከት አዲሱ ሲሆን ዘካርያስ ፍቅሬ ደግሞ በምትኩ ጨዋታውን የጀመረው አጥቂ ነበር።

ተመጣጣኝ በሚመስል እንቅስቃሴ የጀመረው ጨዋታ ቀስ በቀስ የመከላከያዎች የበላይነት የሰፈነበት ነበር። አብዛኛውን ደቂቃ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን መያዝ ያቻሉት መከላከያዎች የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ግን አልሆነላቸውም። የቡድኑ የቅብብል ፍጥነት አናሳ መሆን አልፎ አልፎ አርባምንጮች ይፈጥሯቸው የነበሩ ክፍተቶችን ለመጠቀም የሚያስችል አልሆነም። 7ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ታዬ ከተመስገን ካስትሮ ቀምቶ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ የመጀመሪያው ቢሆንም ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ማብቂያ ላይ ከታፈሰ ሰረካ ተሻምቶ አዲሱ ተስፋዬ በግንባሩ የጨረፈውም ሌላኛው ጥሩ የሚባል የቡድኑ ሙከራ ነበር። ከዚህ ውጪ ግን ወደ መስመሮች እየወጣ ኳስ በመቀበል ጥሩ ለመንቀሳቀስ የሞከረው ምንይሉ ወንድሙ ያደረጋቸው የርቀት ሙከራዎችም ፂዮን መርዕድን የፈተኑ አልነበሩም። ቡድኑ በሚከተለው የ4-4-2 ዳይማንድ አሰላለፍ ውስጥ የአማካይ ክፍሉ የተዘበራረቀ እንቅስቃሴ ለማጥቃት ጥረቱ ስኬታማ አለመሆን ዋነኛ ምክንያት ነበር።

በአመዛኙ በራሳቸው የሜዳ ክልል ላይ ያሳለፉት አርባምንጮች ብርሀኑ አዳሙ ከእንዳለ ከበደ የተቀበለውን ኳስ ወደ ውስጥ አሻምቶ የመሀል ተከላካዩ በረከት ቦጋለ ጥብቅ በሆነ የግንባር ኳስ ከሞከረ በኃላ ይድነቃቸው ኪዳኔ እና ምንተስኖት ከበደ እንደምንም ካወጡበት አጋጣሚ ውጪ ወደ ጎል አልደረሱም። ቡድኑ በተለይ በምንተስኖት አበራ በርካታ ኳሶች ማቋረጥ ቢችልም ጥሩ የሚባሉ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን እንኳን ማግኘት አልቻለም። በዚህም ሶስቱ የፊት መስመር አጥቂዎች የተለየ ተፅዕኖ መፍጠር ሳይችሉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የተደረጉት ለውጦች የቡድኖቹን አጨዋወትም በመጠኑ የቀየሩ ነበሩ። አሰልጣኝ እዮብ ማለ አለልኝ አዘነን በአስጨናቂ ፀጋዬ በመቀየር የቡድናቸውን አሰላለፍ ከተጋጣሚያቸው ጋር አመሳስለዋል። መከላከያዎች ደግሞ አጋማሹ ሲጀመር ሳሙኤል ታዬን አስወጥተው አቤል ከበደን በማገባት የአማካይ ክፍልቸው ቅርፁን እንዲጠበቅ ለማድረግ ሞክረዋል። ጨዋታው በገፋ ቁጥር ግን የቡድናቸው የማጥቃት እንቅስቃሴ ያላስደስታቸው የሚመስሉት አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ጨዋታውን ከጀመሩት አራት አማካዮች ውስጥ ከቴዎድሮስ ታፈሰ በቀር ሳሙኤልን ጨምሮ አማኑኤል ተሾመን እና ዳዊት እስጢፋኖስንም ጭምር ለመቀየር ተገደዋል።

አርባምንጮች በ48ኛው ደቂቃ ከእንዳለ ከበደ እንዲሁም 56ኛው ደቂቃ ላይ ከምንተስኖት አበራ በተነሱ ኳሶች ለብርሀኑ አዳሙ ከተከላካዮች ጀርባ ጥሩ የሚባሉ ኮሶችን ቢጥሉም ይድነቃቸው ፈጥኖ ቦታው ላይ በመገኘት አክሽፎባቸዋል። ከዚህ ውጪ ብቸኛው የአርባምንጭ ሙከራ አለልኝ አዘነ 68ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ ብቻ ነበር። የተሻሉ የሚባሉ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉት መከላከያዎች በምንይሉ ወንድሙ እና ፍፁም ገብረማርያም ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ከሁለም በላይ ግን 61ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ፍፁም ገ/ማርያም ፣ አቤል ከበደ እና በመጨረሻም ዐወል አብደላ ኳሷን ማግኘት ሳይችሉ የቀሩበት አጋጣሚ ቀልብ ይስብ ነበር። ሆኖም ጨዋታው ተገባደደ ተብሎ ሲጠበቅ ምንይሉ ወንድሙ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ አክርሮ የመታውን ኳስ ፍፁም ቢጨርፈው ፅዮን መርዕድ ማዳን ሲችል እዛው ጋር የነበረው ፍፁም አስቆጥሮ ጦሩን ባለድል አድርጎታል።

መከላከያ ባገኘው ውጤት ነጥቡን 22 አድርሶ ወደ 10ኛ ደረጃ ከፍ ሲል አርባምንጭ ከተማ ደግሞ በነበረበት 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ – መከላከያ

የእግር ኳስ አጋጣሚ እንደዚህ ነው። ነገር ግን ዛሬ የጠበኩትን ያህል አልተንቀሳቀስንም። ብዙ የሚቆራረጡ ኳሶች ነበሩ። ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል የምንደርስበት መንገድም መልካም አልነበረም። ቢሆንም ማሸነፋችን በጣም ትልቅ ነገር ነው። ያሸነፍነው የቅርብ ተፎካካሪያችንን መሆኑ ደግሞ ድሉን ይበልጥ ወሳኝ ያደርገዋል። ከምንም በላይ ማሸነፋችን ለተጨዋቾቼ መነሳሳትን ይፈጥራል። በጥቅሉ በጣም ደስ ብሎኛል።

አሰልጣኝ እዮብ ማለ – አርባምንጭ ከተማ

የዳኛውን ውሳኔ እቀበላለው ግን የስታድየሙ ሰዐት እንደሚያሳየው ጭማሪ ደቂቃው ካለፈ በኃላ ነው ግብ የተቆጠረብን። አቻ የወጣነውን ጨዋታ ተሸንፋቸዋል ተብለናል። ያገኘነውን አጋጣሚ አልተጠቀምንም እንጂ ኳሱን ተቆጣጥረን ብልጫ ይዘን ተጫውተናል። በዳኝነቱ ዙሪያ ብዙ ብናገር ቅጣት ይመጣብኛል። የቤተሰብ ሀላፊ ስለሆንኩ መቀጣት አልፈልግም።