ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛው ሳምንት የደርቢነት ስሜት ከሚንፀባረቅባቸው ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ዛሬ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ተካሂዶ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡ 

በተለምዶ በሲዳምኛ ሩዱዋ (የወንድማማቾች ጨዋታ) የሚል ስያሜ ያለው ይህ ጨዋታ ዛሬ ከመካሄዱ አስቀድሞ የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች በአመራሮቻቸው አማካኝነት ጨዋታው በሰላም እንዲጠናቀቅ መልዕክት በማስተላለፍ ቢጀመርም በስተመጨረሻ ግን የተባለው በተግባር ላይ ሳይውል ተመልክተናል።

እንደተለመደው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ህዝብ መዝሙር ታጅቦ ከተያዘለት ሰአት አስር ደቂቃን ያህል ዘግይቶ በኃይለየሱስ ባዘዘው መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በ5 ቢጫ ካርድ በዛሬው ጨዋታ ላይ ማረፍ እያለበት ተሰልፏል በማለት ክስ አስይዘዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች በተሻለ መልኩ መንቀሳቀስ የቻሉበት እና ሀዋሳ ከተማዎች ከወትሮው እንቅስቃሴያቸው ተቀዛቅዘው የቀረቡበት ነበር። ሲዳማዎች በተለይ በሁለቱም መስመሮች ሐብታሙ ገዛኸኝ እና አዲስ ግደይ ላይ የተመሰረተ የማጥቃት እንቅስቃሴውን ሲያደርግ ሀዋሳዎች እንደተለመደው ከተከላካይ መስመሩ ፊት የሚገኙት ጋብሬል እና ሙሉዓለም ላይ ማዕከል ያደረገ እንቅስቃሴ አድርገዋል።

ኃይል በቀላቀለ አጨዋወት እና በሚቆራረጡ ቅብብሎች በጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያን የግብ አጋጣሚን ለማየት የቻልነው ገና በ1ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ከቅጣት ምት ወንድሜነህ አይናለም በግራ በኩል የተገኘችውን እድል አክርሮ በመምታት ሞክሮ ሶሆሆ ሜንሳህ ይዞበታል። በሀዋሳ በኩል ደግሞ 6ኛው ደቂቃ ላይ ጋብሬል አህመድ ከርቀት አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ አውጥቶበታል። ቀጣይ ሙከራ ለመመልከት ረጅም ደቂቃ የፈጀ ሲሆን 26ኛው ደቂቃ ላይ ሐብታሙ ገዛኸኝ ወደ ሳጥን ገብቶ ወደ ግብ የላካትን ኳስ የእለቱ ዋና ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ረዳት ዳኛው ምልክት ሳያነሱ ከጨዋታ ውጭ ነው በማለታቸው በርካታ የሲዳማ ቡና ተጫዋቾችን ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ በር ከፍተዋል፡፡

በእንቅስቃሴ ረገድ ሲዳማዎች የተሻሉ ቢሆኑም ግብ የማስቆጠር ጥረት በማድረጉ ረገድ ሀዋሳዎች በአንፃራዊነት የተሻሉ ነበሩ። 29ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ታፈሰ ሰለሞን ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ ሲይላ መሐመድ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ላይ የወጣችበት እንዲሁም 40ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን ከታፈሰ ሰለሞን ጋር በአንድ ሁለት ንክኪ ወደ ግብ ክልል በመድረስ ታፈሰ ሞክሮ ለጥቂት የወጣችበት ሙከራዎች ለዚህ እንደ አብነት የሚጠቀሱ ነበሩ። በሲዳማ በኩል ደግሞ ወንድሜነህ ዓይናለም በሁለት አጋጣሚዎች በ35ኛው ደቂቃ ከዮናታን ፍሰሀ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ የወጣበት እና ከቅጣት ምት በቀጥታ ሞክሮ ሶሆሆ ያወጣበት አጋጣሚዎች የሚጠቀሱ ናቸው።

በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማዎች የቢጫ ካርድ የተመለከተውን ተከላካይ ላውረንስ ላርቴን በፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል። ወደሚታወቁበት የኳስ ቅብብል የተመለሱት ሀዋሳዎች በተሻለ ሁኔታ ሲንቀሳቀሱ በተወሰነ መልኩ የተዳከሙ የመሰሉት ሲዳማዎችም በአዲስ ግደይ ፊት አውራሪነት የባለሜዳዎቹን ተካላካይ ክፍል ማስጨነቃቸው አልቀረም።

በዚሁ አጋማሽ ጅማሮ ከታዩት ሙከራዎች ውስጥ የሀዋሳው ፍቅረየሱስ ከቀኝ በኩል ያሻገራት እና ታፈሰ ሰለሞን ለእስራኤል ሰጥቶት እስራኤል ከግብ ጠባቂው አላዛር መርኔ ጋር ተገናኝቶ ያመከናት እንዲሁም በሲዳማ በኩል 55ኛው ደቂቃ ላይ ሐብታሙ ገዛኸኝ ከርቀት በቀጥታ የመታው እና ሶሆሆ እንደምንም ያዳነበት ኳስ ይጠቀሳሉ። ከሁለተኛው ሙከራ አራት ደቂቃዎች ቀደም ብሎ ግን የሀዋሳ ከተማው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳህ ኳስ ሊያሻማ ሲል ጋርዶኛል በማለት ከወንድሜነህ አይናለም ጋር በፈጠሩት ሰጣ ገባ የዕለቱ ዋና ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ሁለቱንም በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወግደዋቸዋል። ሶሆሆ ሜንሳህን የሚተካው ግብ ጠባቂ አላዛር መርኔን በሙሉዓለም ረጋሳ ቀይሮ ለማስገባትም ጨዋታው 12 ያህል ደቂቃ ዘግይቶ ነበር የጀመረው። ሜንሳህ ሜዳ ለቆ በመውጣት ላይ ሳለ የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች የውሀ መያዣ ኮዳዎችን በተጫዋቹ ላይ ሲወረውሩም ታዝበናል፡፡

ከቆመበት በቀጠለው ጨዋታ 70ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን በግምት ከ40 ሜትር ርቀት ላይ ሳይጠበቅ አክርሮ የመታውን ኳስ መሳይ አያኖ እንደምንም አውጥቶበታል። 73ኛው ደቂቃ ላይ ግን ኄኖክ ድልቢ ከጋብሬል እና ፍቅረየሱስ ጥምረት የተገኘውን ኳስ ለእስራኤል አሸቱ አቀብሎት እስራኤል አጋጣሚውን ወደ ግብነት ቀይሮ ሀዋሳን ቀዳሚ አድርጓል። ከግቧ በኃላ የመልሶ ማጥቃትን ምርጫቸው ያደረጉት ሀዋሳዎች በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች በሲዳማ ቡና የበላይነት ሲወሰድባቸው ታይቷል። ነገር ግን እነኚህ ደቂቃች በሁለቱም ቡድኖች በኩል ከባድ ሙከራዎች የተደረጉባቸው ነበሩ።  83ኛው ደቂቃ ላይ ዮናታን ፍሰሀ አሻምቶት አዲስ ግደይ በግንባር ሞክሮ ለጥቂት የወጣበት ፣ 85ኛው ደቂቃ ፍሬው ከተላከለት ረጅም ኳስ መነሻነት ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖን አልፎ ኢላማውን ያልጠበቀበት እንዲሁም 87ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝን ተክቶ የገባው አብዱለጢፍ መሀመድ በመስመር በኩል ያሻገረለትን ኳስ ትርታዬ ደመቀ በግንባር ገጭቶ ሙከራው የግቡን ብረት ታካ የወጣችበት ተጠቃችሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

የጨዋታው ጭማሪ 8 ደቂቃዎች ሊጠናቀቁ በተቃረቡበት ወቅት ሲላ መሐመድ ኳስ ከግብ ክልሉ ለማራቅ ጥረት ሲያደርግ አዲስ ግደይ ላይ ጥፋት ሰርቷል በሚል የዕለቱ ዳኛ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል። ፍፁም ቅጣት ምቱን አዲስ ግደይ ራሱ ወደ ግብነት ለውጦ ክለቡን ከሸንፈት ማዳን ችሏል ፡፡  በውሳኔውም የዕለቱ ዳኛ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ የታየ ሲሆን የሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች እርስ በእርሳቸው የውሀ መያዣ ኮዳዎችን በመወራወር የጨዋታውን ገፅታ የሚያበላሹ ድርጊቶችን ሲፈፅሙ የታየ ሲሆን ጨዋታውም 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል ፡፡ ከጨዋታው በኃላ የሀዋሳ ከተማው ግብ ጠባቂ እና የሲዳማ ቡናው አማካይ ዮሴፍ ዮሀንስ ለድብድብ ተጋብዘው በሜዳ ላይ ያሳዩት አስነዋሪ ድርጊትም የዛሬው ጨዋታ ሌላው ክስተት ነበር፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

ም/አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ

ጨዋታው ከመጀመሪያው ጀምሮ የደርቢ በመሆኑ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ለመጫወት አስበን ነበር። 4-5-1 አጨዋወትን ተጠቅመን ነበር የገባነው። የነርሱ አጥቂዎች ይሸሻሉ ብለን አላሰብንም። ከዕረፍት በኃላ በንታወቅበት 4-3-3 ተመልሰናል ፤ ጎልም አስቆጥረናል። ከዛ ደግሞ ተቆጥሮብናል። ያው ሰበብ ባይሆንም የተሰጠብን ፍፁም ቅጣት ምት ግን ተገቢ አልነበረም።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

ከእረፍት በፊት ያሰብነውን አድርገናል። ወንድሜነህ በቀይ ከወጣ በኃላ ግን መሀላችን ልክ አልነበረም። ምንፈልገውን ግን አግኝተናል ተግነን በመጫወታችንም ፍፁም ቅጣት ምት ማግኘት ችለናል።