የሲዳማ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ የቦታ ለወጥ ተደርጎበታል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ይርጋለም ላይ እንደሚካሄድ ይጠበቅ የነበረው የሲዳማ ቡና እና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በባለሜዳው ሲዳማ ቡና ጥያቄ መሰረት የቦታ ለወጥ ተደርጎበታል።

የሲዳማ ቡና ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ ሳሳሞ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደተናገሩት ” ከዚህ ቀደም የኛ ሜዳ ይርጋለም ነበር። ከድሬዳዋ ጋር በምናደርገው ጨዋታ ላይ ግን የቦታ ለውጥ አድርገን ወደ ሀዋሳ ወስደነዋል። ምክንያቱም የሲዳማ ፍቼ ጨምበላላ በአል የሚከበርበት ወቅት በመሆኑ እና ሀዋሳ ላይ ስለሚከበርም ለበዓሉ ድምቀት ሲባል የቦታ ለውጡ በማስፈለጉ ነው። በቀጣይ በሚኖሩ ጨዋታዎች ግን እንደተለመደው ወደ ይርጋለም የምንመለስ ይሆናል።” ብለዋል።

በመሆኑም በ26ኛው ሳምንት ሲዳማ ቡና ድሬዳዋ ከተማን ሰኞ በ9፡00 ሰአት በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታድየም የሚገጥም ይሆናል።