ሲዳማ ቡና ተመስገን ገ/ፃዲቅን ሲያስፈርም ሁለት ረዳት አሰልጣኞችን ሾሟል

በዝውውር መስኮቱ ዘግይቶ ከተቀላቀለ በኋላ በርካታ ተጫዋቾችን እያስፈረመ የሚገኘው ሲዳማ ቡና ተመስገን ገ/ፃዲቅን ሲያስፈርም ለዘርዓይ ሙሉ ረዳቶች ሁለት አሰልጣኞችን ወደ ክለቡ ቀላቅሏል፡፡

በሀዋሳ ከተማን በ2002 ከወጣት ቡድኑ ካደገ በኃላ ለአራት ዓመታት ያገለገለው አጥቂው ተመስገን ገ/ፃዲቅ 2005 ሀዋሳ ከተማን ለቆ ወደ ሲዳማ ቡና ካመራ በኃላ መልካም የሚባል ጊዜያት ማሳለፍ የቻለ ሲሆን 2007 ወደ አዳማ ከተማ እንዲሁም በመሀል ወደ ሀዲያ ሆሳዕና አምርቶ ለግማሽ ወራት መጫወትም ችሏል። ከ2009 እስከተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ደግሞ በመከላከያ አሳልፎ የሲዳማ ቡና 8ኛ ፈራሚ በመሆን ወደ ቀድሞ ክለቡ ሲዳማ ቡና በሁለት ዓመት የውል ስምምነት ተቀላቅሏል፡፡

በተያያዘ ዜና ሲዳማ ቡና ሁለት ምክትል አሰልጣኞችን ሾሟል። የቀድሞው የደቡብ ፖሊስ፣ ወራቤ ከተማ እና ኢትዮጵያ ውሀ ስራ አሰልጣኝ የነበረው ያሬድ ገመቹ የክለቡ ምክትል አሰልጣኝ በመሆን ሲሾም ሌላኛው ደግሞ በክለቡ በሴቶች ቡድን ውስጥ በምክትል አሰልጣኝነት ከዚህ ቀደም የሰራው እንዲሁም ያለፈውን አንድ ዓመት ደግሞ በነቀምት ከተማ ምክትል ሆኖ የሰራው ስንታየሁ ግድየለውን የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል፡፡