ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መከላከያ ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ

ላለፉት ሦስት ቀናት ስድስት ጨዋታዎች በተደረጉበት የኢትዮጵያ ፕሪምየት ሊግ አምስተኛ ሳምንት ዛሬ መከላከያ እና ወልዋሎ ዓ.ዩ ይገናኛሉ። ጨዋታውን እንደተለመደው በቅድመ ዳሰሳችን ተመልክተነዋል። 

ፍፁም አስቸጋሪ በነበረው የ2010 የውድድር ዓመት የተከሰቱ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች ሲነሱ የሚያዚያ 22ቱ የመከላከያ እና ወልዋሎ ጨዋታ አብሮ ይነሳል። ከዚያ አሳዛኝ ምሽት በኋላም ሁለቱ ክለቦች በአዲሱ የውድድር ዓመት የሚገናኙበት የመጀመሪያ ጨዋታ ዛሬ 11፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ይደረጋል። 

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ሽንፈት የደረሰበት መከላከያ በሊጉ አንድ ጨዋታ ብቻ ያደረገ ክለብ ነው። በመጀመሪያው ሳምንት ሀዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስን ገጥሞ 2-1 መርታት የቻለው መከላከያ ሦስት ጨዋታዎችን ካደረገው የዛሬው ተጋጣሚው እኩል ነጥቦችን መያዝ ችሏል። በተመሳሳይ ደቡብ ፖሊስን አሸንፎ ሦስት ነጥቦችን ያሳካው ወልዋሎ ከዚያ አስቀድሞ በሀዋሳ ከተማ እና መቐለ 70 እንደርታ በድምሩ አምስት ግቦች ተቆጥረውበት ለሽንፈት ተዳርጎ ነበር። ከሁለቱ ክለቦች በዛሬው ጨዋታ ድል የቀናው ቡድን ነጥቡን ስድስት በማድረስ እስከ አምስት ወይንም ስድስተኛ ደረጃ ከፍ የማለት ዕድል ይኖረዋል። 

የመከላከያው አማካይ ቴዎድሮስ ታፈሰ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ላይ በተመለከተው ቀይ ካርድ ምክንያት ቅጣት ላይ ሲገኝ ከጉዳቱ በማገገም ቀላል ልምምድ የጀመረው ተመስገን ገብረኪዳንም የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። አስራት መገርሳ ፣ ዳንኤል አድሀኖም ፣ ኤፍሬም ኃይለማርያም እና ዳዊት ፍቃዱ ደግሞ በወልዋሎ ዓ.ዩ በኩል ጉዳት ላይ በመገኘታቸው ጨዋታው የሚያልፋቸው ተጫዎቾች ናቸው።

በጨዋታው የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ የተመሰረተ አጨዋወት የሚተገብሩት ሁለቱ ቡድኖች መሀል ሜዳ ላይ ወሳኝ ፍልሚያ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። በዳዊት እስጢፋኖስ የሚመራው የመከላከያ አማካይ ክፍል የመስመር ተከላካዮቹን በሚያሳትፈው አጨዋወቱ ወደ ወልዋሎ ሜዳ አመዝኖ ጫና በመፍጠር እንደሚያጠቃ ይታሰባል። በሌላ በኩል የቴዎድሮስ ታፈሰ አለመሰለፍ መከላከያ ቀጥተኛ ኳሶችን ወደ ወልዋሎ ሳጥን የሚጥልባቸውን አጋጣሚዎች መቀነሱ የማይቀር ነው። በመሆኑም የቡድኑን አጥቂዎች ከነደስታ ደሙ ጋር የሚያፋልሙባቸው ቅፅበቶች በአመዛኙ ከአጫጭር ቅብብሎች የሚመነጩ ይሆናሉ። እንደ አምናው ሁሉ በደቡብ ፖሊሱ ጨዋታ የዋለልኝ እና አፈወርቅን የመሀል ሜዳ ጥምረት የተጠቀመው ወልዋሎም ከጦሩ ጋር የሚጠብቀውን የመሀል ሜዳ ፍልሚያ ካለፈ በኤፍሬም አሻሞ እና አብዱርሀማን ፉሰይኒ በኩል ጥቃት የሚሰነዝርበት አግባብ እንደሚኖር ይገመታል። ይህም የቡድኑ የመስመር አጥቂዎች ከሽመልስ ተገኝ እና የቀድሞ አጋራቸው ዓለምነህ ግርማ ጋር የሚጠብቃቸውን ትንቅንቅ ተጠባቂ ያደርገዋል። 

የእርስ በስርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ወልዋሎ ዓ.ዩ አምና ሊጉን ሲቀላቀል  የተገናኙባቸው ሁለት ጨዋታዎች በመከላከያ አሸናፊነት የተጠናቀቁ ነበሩ። በጨዋታዎቹ መከላከያ ሦስት ጊዜ ወልዋሎ ደግሞ አንድ ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።

– የመከላከያው አጥቂ ምንይሉ ወንድሙ ዓዲግራት እና አዲስ አበባ ላይ በተደረጉት ጨዋታዎች ጎል ሲያስቆጥር ሁለቱም ጎሎች የተመዘገቡት ሠላሳ ሦስተኛው ደቂቃ ላይ ነበር። 

– ሁለቱም ክለቦች በሊጉ እስካሁን የያዟቸው ሦስት ነጥቦች የተገኙት አዲስ አዳጊው ደቡብ ፖሊስን በመርታት ነበር።

ዳኛ 

– ከከፍተኛ ሊግ ካደጉ ዳኞች መካከል አንዱ የሆነው ባህሩ ተካ በዚህ ጨዋታ የፕሪምየር ሊግ ስራውን ይጀምራል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-4-2 ዳይመንድ)

አቤል ማሞ

ሽመልስ ተገኝ – አዲሱ ተስፋዬ – አበበ ጥላሁን – ዓለምነህ ግርማ

በሀይሉ ግርማ

ሳሙኤል ታዬ – ፍሬው ሰለሞን

ዳዊት እስጢፋኖስ

ፍፁም ገብረማርያም – ምንይሉ ወንድሙ 

ወልዋሎ ዓ.ዩ (4-3-3)

አብዱልዓዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን –  ደስታ ደሙ – ቢኒያም ሲራጅ – ብርሀኑ ቦጋለ

ዋለልኝ ገብሬ – ብርሀኑ አሻሞ – አፈወርቅ ኃይሉ

አብዱርሀማን ፉሴይኒ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ኤፍሬም አሻሞ