የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 1-0 ሲዳማ ቡና

ከጅማ አባጅፋርና ከሲዳማ ቡና ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን እንደሚከተለው ሰጥተዋል።

” የአጨዋወት ስልታችንን ከቀየርን ወዲህ ውጤታማ እየሆንን እንገኛለን” የሱፍ ዓሊ (ጅማ አባ ጅፋር )

ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ስላሳየው መሻሻል

ከመጀመሪያው ዙር ስንጠቀምበት የነበረውን አጨዋወት ከቀየርን ወዲህ ውጤታማ እየሆንን እንገኛለን። የቀየርነውን የአጨዋወት ስልት ለመላመድ በተደጋጋሚ እየሰራን እንገኛለን። አሁን እየተላመዱት ስለሆነ በቀጣይ የተሻለ ነገር እንሰራለን። ተጨዋቾቻችን ላይ ተነሳሽነት ፈጥረናል። በመጀመሪያው ዙር ባሳየነው ወጣ ገባ አቋም ተጫዋቾቹ ተቆጭተዋል። ይህን በማስተካከል ደጋፊዎችን ለመካስ እየሰራን ነው። በዛሬው ጨዋታ እነሱ ኳስን ማንሸራሸር ላይ ነበር ትኩረታቸው። እኛ ደግሞ ውጤት ላይ የዛሬው ጨዋታ ልዩነት ይህ ነበር።

“ከሜዳ ውጭ በምናደርጋቸው ጨዋታዎች የዳኝነት ተፅዕኖዎች ከባድ እየሆነብን መጥቷል” ዘርዓይ ሙሉ (ሲዳማ ቡና)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ላይ ጥሩ ነበርን፤ ጥሩ ተቀሳቅሰናል። ብልጫም ወስደናል። ማሳበብ አይደለም ከሜዳ ውጭ በምናደርጋቸው ጨዋታዎች የዳኝነት ተፅዕኖዎች ከባድ እየሆነብን መጥቷል። በእያንዳንዱ ንክኪ ይነፋል ይህ ደግሞ የኛን ተጫዋቾች እቅስቃሴ ያወርደዋል። ከጅማሬው አስቶ አስከ ፍፃሜ በዳኝነት ደስተኛ አይደለሁም። ስለዳኝነት ማንሳት ሰልችቶኛል። እንደቡድን የተሻለ ተቀሳቅሰናል። እነሱ በረጃጅም ኳሶች ለመጫወት ሞክረዋል። በዛም ውጤታማ አልነበሩም። በአቋቋምና በማርኪንግ ችግር ምክንያት ጎሉ ተቆጠረብን እንጂ ጨዋታው ላይ ጥሩ ነበርን ።

ወደዚህ ስንመጣ በቂ ትራንስፖርት አላቀረቡልንም። በባጃጅ ነበር ወደ ልምምድ ቦታ የምንቀሳቀሰው ልምምድ ቦታ አልተፈቀደልንም አንድ ጊዜ ብቻ ነው ሜዳው ላይ የሰራነው። የቀረውን እርሻ ላይ ነው እንድንለማመድ ያደረጉን። ይህ ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ ነው።

የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ወደ ግብ እድል አለመቀየር

የመረጥነው አጨዋወት ነው። ጎላችንን ሸፍነን ወደ ፊት ለመሄድ ነበር ያቀድነው ሙከራዎቻችን ኢላማቸውን ባይጠብቁም በተደጋጋሚ ወደ ጎል ለመድረስ ሞክረናል። እነሱም ወደፊት ለመሄድ ሲሞክሩ ከኛ የተሻለ ጎል ጋር መድረስ አልቻሉም ፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡