“ከሩዋንዳው ጨዋታ በፊት ያሉብንን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ለመለየት የነገውን ጨዋታ እንጠቀምበታለን” አብርሃም መብራቱ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የነገው የወዳጅነት ጨዋታን እና አጠቃላይ የቡድኑ ሁኔታ አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ስለ ወዳጅነት ጨዋታው?

“ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ይህንን የወዳጅነት ጊዜ ጨዋታዎች ሳትጠቀም ቆይታለች። እኛ ደግሞ ፊፋ የፈቀደውን የወዳጅነት ጨዋታዎች ወቅትን በመጠቀም ጨዋታ እናደርጋለን ብለን ቃል በገባነው መሰረት ጨዋታ አግኝተናል። በመጀመሪያ ከፌደሬሽናችን ጋር በመሆን ከሶስት ሃገራት ጋር ግንኙነት አድርገን ነበረ። እነዚህም ሃገራት በሜዳቸው ሄደን ጨዋታ እንድናደርግ ቢፈቅዱም ለሩዋንዳው ጨዋታ ዩጋንዳን መርጠናል። የወዳጅነት ጨዋታ ከሃገራችን ወተን እንዳናደርግ ያደረገን የፌደሬሽናችንም የአቅም ውስንነት ነው። በዚህ አጋጣሚ መንግስት እና የሚመለከታቸው አካላት በዚህ ጉዳይ ድጋፍ ቢያደርጉልን እና ጨዋታዎችን ብናደርግ ደስ ይለናል።”

ወዳጅነት ጨዋታውን ለቡድን ውህደት ነው የምትጠቀሙት ወይንስ ቋሚ 11 ለመምረጫነት?

“የወዳጅነት ጨዋታ ለሁለት ነገሮች ሊጠቅም ይችላል። አንደኛው ከጨዋታ በፊት ያሉትን ደካማ እና ጠንካራ ጎኖች እንድታይ ሁለተኛ ደግሞ በውጪ ሃገራት የሚጫወቱ የቡድኑ ተጨዋቾችን እያመጣት ቡድኑን ለመገንባት። አሁን እኛ የነገው ግጥሚያ ከሩዋንዳው ጨዋታ በፊት ያሉንን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች የምናይበት መስታወት እንዲሆን ነው የፈለግነው። የምንወዳደርበት ውድድር ደግሞ በሃገር ውስጥ ተጨዋቾች የሚደረግ እንደመሆኑ ሁለተኛውን መንገድ አልተጠቀምንም። ስለዚህ ለቻን ውድድር የሚጠቅሙንን ተጨዋቾች ለመለየት ነው የነገውን ጨዋታ የምንጠቀምበት።

ስለ ቡድኑ ውጤት ማጣት?

“ባለፉት ውድድሮች ውጤት ለማምጣት የምንሞክረው ጨዋታዎቹን እያደረግን ነው እንጂ ከመጀመሪያም ቃል ገብተን አልነበረም። ከነዚህ ውድድሮች በመቀጠል ደግሞ የቻን ውድድር ነው የመጣው፤ ይህንንም በአግባቡ እያከናወንን እንገኛለን። ጅቡቲን በደርሶ መልስ አሸንፈናል፣ ከዛ የገጠምነው ሌሶቶንም በደርሶ መልስ አሸንፈን የዓለም ዋንጫ ማጥሪያ ምድብ ድልድል ውስጥ ገብተናል፤ ከብዙ ችግሮች ጋር ተዳምሮም ቢሆን። ባደረግናቸው ጨዋታዎች ሜዳችን ላይ ብልጫ አልተወሰደብንም። በሩዋንዳም ስንሸነፍ ብልጫ ነበረን፤ ነገር ግን ግብ ማስቆጠር አልቻልንም። ስለዚህ ቡድኑ በግብ ማግባት ችግር ነው በሩዋንዳውም ጨዋታ የተሸነፈው። ሌላው መረሳት የሌለበት ነገር ቡድኑ አዲስ መሆኑ ነው። 85% ቡድኑ በወጣቶች ነው የተገነባው እነሱ ደግሞ ጊዜ ይፈልጋሉ።”

ለሩዋንዳው የመልስ ጨዋታ ምን ታስቧል?

“ከሩዋንዳው ጨዋታ በፊት ያሉብንን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ለመለየት የነገው ጨዋታ እንጠቀማለን። ስለዚህ ለሩዋንዳው ጨዋታ ከዛ ተነስተን ጥሩ ዝግጅት እናደርጋለን።”

ስለተሰጣቸው የዝግጅት ጊዜ?

“ይሄ ከአቅም ጋር የሚያያዝ ነው። እንደሚታወቀው ተጨዋቾቹ ረፍት ላይ ናቸው ሊግ ስለሌለ። ብዙ ሰው ደግሞ ይህንን እያነሳ ለምን ቶሎ ተጠርተው ዝግጅት አይጀመርም ሲል ነበረ። ነገር ግን እነዚህ ተጨዋቾች አመቱን ሙሉ ሲጫወቱ ስለቆዩ እረፍት ያስፈልጋቸዋል። ሰዎች ስለሆኑ አርፈው እንዲመጡ ማድረጋችን አግባብ ነው ብዬ አስባለሁ።”

በዝግጅት ጊዜ ቡድኑ ስላጋጠሙት ነገሮች?

“ምንም ፈተና አላጋጠመንም። ባህር ዳር ከገባን ጀምሮ መልካም አቀባበል ተደርጎልናል። ከዚህ በተጨማሪ ሜዳዎች ተፈቅደውልን ልምምዳችንን ሰርተናል። ያረፍንበት ሆቴልም ጥሩ ነው። እንደውም በዚህ አጋጣሚ የባህር ዳር እና አካባቢውን የስፖርት አፍቃሪ ነገ ስታዲየም እንዲገና እና እንዲያበረታትን እንደዚሁም ሌሴቶን በደርሶ መልስ አሸንፈን ወደ ዓለም ዋንጫ የማጣሪያ የምድብ ድልድል በመግባታችን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ከጀርባችን ሆነው ስለነበረ።”

ስለ ጉዳት?

“ያሬድ ብቻ ነው ከስብስቡ ውጪ የሆነው። ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው ደግሞ መጠነኛ ጉዳት ስላጋጠመው ሙሉ በሙሉ ልምምድ ውስጥ አልገባም። በአጠቃላይ ግን ሌሎቹ ተጨዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ