ሴቶች 2ኛ ዲቪዚዮን | ቦሌ እና ፋሲል ከሜዳቸው ውጪ፤ ባህር ዳር እና ልደታ በሜዳቸው አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን አራተኛ ሳምንት ዛሬ በአራት ጨዋታዎች ሲቀጥል መሪውን ሻሸመኔ በባህርዳር ሽንፈት ገጥሞታል። ቦሌ እና ፋሲል ከሜዳቸው ውጪ ሲያሸንፉ ልደታም ድል አስመዝግቧል።
ለገጣፎ ለገዳዲ 0-4 ቦሌ ክ/ከተማ

(ዳንኤል መስፍን)

በእንቅስቃሴ ደረጃ ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረው ጨዋታ እንግዶቹ ቦሌዎች በአንፃራዊነት በመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ሆነው ሲታዮ ገና በ8ኛው ደቂቃ ነበር ከመሐል ሜዳ አደራጅተው ወደ ቀኝ መስመር ባመራው ኳስ ቤተልሔም ምንታለም ወደ ጎል ያሻገረችውን ሜሮን አበበ ወደ ጎልነት በመቀየር ቦሌዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች።


ጨዋታው ቀጥሎ ለገጣፎዎች በሁለት አጋጣሚ ነፃ የማግባት አጋጣሚዎች አግኝተው ሳይጠቀሙ መቅረታቸው ተጨማሪ ጎሎች እንዲቆጠርባቸው ሆኗል። በተለይ የለገጣፎዋ አጥቂ ቤቴልሔም ስለሺ የቦሌዋን ግብጠባቂ በማለፍ ሳትጠቀምበት የቀረችው ኳስ የሚያስቆጭ ነበር።
ተረጋግተው በመጫወት ጎል የሚያስቆጥሩበትን አጋጣሚ ለመፍጠር የተንቀሳቀሱት ቦሌዎች በ37ኛው ደቂቃ ሳይጠበቅ ተከላካይዋ ካምላክነሽ ሀንቁ ከርቀት ባስቆጠረችው ጎል መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል። ብዙም ሳይቆይ 41ኛው ደቂቃ በግሩም ሁኔታ ለቦሌዎች ሦስተኛ ጎል መዓዛ አብደላ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ አስቆጥራለች።

ከእረፍት መልስ ከመጀመርያው አጋማሽ ከነበራቸው ደካማ እንቅስቃሴ በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ባለሜዳዎቹ ለገጣፎዎች ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አለመፍጠራቸው ወደ ጨዋታው ለመመለስ የነበራቸውን ሥራ አክብዶባቸዋል። በአንፃሩ ቦሌዎች ጨዋታውን እየመሩ እንደመሆናቸው መጠን ተረጋግተው በመጫወት የሚገኙትን የማግባት አጋጣሚ ለመጠቀም ያደረጉት እንቅስቃሴ ተሳክቶላቸው በ75ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተላከውን ኳስ በዕለቱ ጥሩ ስትንቀሳቀስ የተመለከትናት ንጋት ጌታቸው አራተኛ ጎል በግንባሯ በመግጨት አስቆጥራለች። በመጨረሻም በቀሩት ደቂቃዎች እምብዛም የተለየ ነገር ሳንመለከት ጨዋታው በእንግዶች ቦሌዎች 4–0 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።

ባህር ዳር ከተማ 1-0 ሻሸመኔ ከተማ
(ሚካኤል ለገሰ)

ረጃጅም ኳሶች የበዙበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራዎች እምብዛም ሳይስተናገዱበት ተከናውኗል። በጨዋታው ጅምሮ በአንፃራዊነት የተሻሉ የነበሩት ባህር ዳር ከተማዎች በ10ኛው ደቂቃ ቤተልሄም ግዛቸው ከቅጣት ምት የተገኘን ኳስ በቀጥታ መትታ በሞከረችው ኳስ የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል። በተቃራኒው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ግብ ማስተናገድ የፈለጉ የማይመስሉት ተጋባዦቹ ወደ ራሳቸው የሜዳ ክፍል በመጠጋት ጨዋታውን ጀምረዋል። ምንም እንኳን ቡድኑ ወደ ራሱ የግብ ክልል ቢያፈገፍግም ረጃጅም ኳሶችን እና የቆሙ ኳሶችን በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ጥሯል። በ18ኛው ደቂቃም ከርቀት የተመታን ኳስ የባህር ዳር ከተማ ተከላካይ በግምባሯ ስትገጨው ያገኘችው ዓለሚቱ ድሪባ ጥሩ ሙከራ ሰንዝራ መክኖባታል።

በአሰልጣኝ ሰርካዲስ እውነቱ የሚሰለጥኑት የባህር ዳር ከተማ ተጨዋቾች በ33ኛው ደቂቃ በትዕግስት ወርቄ አማካኝነት ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ አድርገዋል። በዚህ ደቂቃ ትዕግስት በቀኝ መስመር ያገኘችውን ኳስ እየገፋች ሄዳ የሞከረቸው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው እየተመለሱ የመጡት ሻሸመኔዎች በ35 እና 36ኛው ደቂቃ ለግብነት የቀረበ ጥቃት ሰንዝረዋል። በእነዚህ ተከታታይ ደቂቃዎች የተገኘን አጋጣሚ ሜሮን ገገሞ ከሳጥን ውስጥ እና ውጪ አክርራ በመምታት ቡድኗን መሪ ለማድረግ ጥራ ነበር።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በቀሩት የጭማሪ ደቂቃዎች ባህር ዳር ከተማዎች ሁለት ጥሩ እድሎችን በትዕግስት አማካኝነት ፈጥረው የሻሸመኔ ግብ ጠባቂ ፅዮን ግርማ እና የግቡ አግዳሚ አምክኖባቸዋል። የመጀመሪያው አጋማሽም ምንም ጎል ሳይስተናገድበት 0-0 ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ጨዋታውን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠሩት ባህር ዳሮች ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ጀምረዋል። አጋማሹ በተጀመረ በ5ኛው ደቂቃም ሰብለወንጌል ከመዓዘን የተሻገረን ኳስ በግምባሯ በመግጨት ሙከራ አድርጋለች። ከ3 ደቂቃዎች በኋላም ዳሳሽ ሰውአገኝ ከሻሸመኔ ግብ ጠባቂ ጋር 1ለ1 የተገናኘችበትን ኳስ አግኝታ ግብ አስቆጥራለች። የሚፈልጉትን ገና በአጋማሹ ጅማሮ ያገኙት ባለሜዳዎቹ ቀስ በቀስ እየተቀዛቀዙ ታይተዋል።

በተቃራኒው አጋማሹን በጥሩ ብቃት ያልጀመሩት ሻሸመኔዎች ግብ ካስተናደጉ በኋላ የተሻለ ለመንቀሳቀስ ጥረዋል። በ69ኛው ደቂቃም አለሚቱ በግራ መስመር ያገኘችውን የቆመ ኳስ በቀጥታ መትታ ግብ ለማስቆጠር ሞክራለች። ከዚህ ጥሩ ሙከራ በተጨማሪ ቡድኑ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ እጅግ ለግብነት የቀረበ ሙከራ አድርጎ መክኖበታል። ጨዋታው በሚፈልጉት መንገድ እየቀጠለላቸው ያለው ባህር ዳር ከተማዎች በ81ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችውን ትዕግስት ወርቄ በሁለት ቢጫ አጥተዋል። ተጨዋቿ ከሜዳ ከተወገደች እና የቁጥር ብልጫ ከተወሰደባቸው በኋላም ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብተው ተጫውተዋል።

በ85ኛው ደቂቃ ተቀይራ የመወደ ሜዳ የገባችው አምሳል ፍስሃ ጥሩ ኳስ ከርቀት አክርራ መትታ ቡድኗን አቻ ለማድረግ ብትጥርም ኳስ እና መረብ ሳይገናኝ ቀርቷል። ይህንን ጥሩ ሙከራ ያደረገችው አምሳል ከ2 ደቂቃዎች በኋላም ሌላ ኳስ ከመስመር ወደ ግብ መትታ ወጥቶባታል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረውም ተጋባዦቹ ተጨማሪ ሙከራ በወለላ ባልቻ አማካኝነት ፈጥረው ወጥቶባቸዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በባህር ዳር ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ሁለት ጨዋታዎች ተከናውነዋል። በ9:00 የተገናኙት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ሲሆኑ እንግዶቹ 2-1 አሸንፈዋል። ቂርቆሶች በአዳነች በቀለ ጎል የመጀመርያውን አጋማሽ በመሪነት ቢያጠናቅቁም ከዕረፍት መልስ ተሻሽለው የገቡት ፋሲሎች በአብስራ ይታየው እና ረድኤል ዳንኤል ጎሎች ማሸነፍ ችለዋል።

ቀጥሎ የተካሄደው የልደታ ክፍለ ከተማ እና ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ጨዋታ በልደታ 2-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ የወጣቶቸ አካዳሚ እና ንፋስ ስልክ ጨዋታ አካዳሚ ለሴቶች ብሔራዊ ቡድን በርካታ ተጫዋቾች በማስመረጡ ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ