የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጉዳይ ዛሬ ውሳኔ ያገኝ ይሆን ?

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ዛሬ ያደርጋል።

እጅግ የተንዛዛው እና ብዙዎች እንዲወያዩበት ካስቻሉ ወቅታዊ መነጋገሪያ ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአሰልጣኝ ቅጥር ጉዳይ ይጠቀሳል፡፡ ፌዴሬሽኑ ባለፈው ዓመት ወርሀ ሐምሌ ላይ በሁሉም እርከን ላሉ አሰልጣኞች ውል አላድስም በማለት በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ማሳወቁም የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ ሆኖም ካፍ ከወር በፊት የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች በጥቅምት ወር እንደሚከናወኑ ይፋ በማድረጉ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም አሰልጣኝ አልባ ከመሆኑ አኳያ የውድድሩ ቀን እየቀረበ በመሆኑ በርካቶችን እያሳሰበ ይገኛል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለአሰልጣኝ ቅጥር እና ለወደፊት እቅዶች የመንግሥትን ምላሽ እየጠበቀ እንደሆነ መግለፁ የሚታወስ ሲሆን በቅርቡ የጤና ሚኒስቴር በሀገሪቱ የሚደረጉ ክንውኖች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ መከናወን እንደሚችሉ ማስታወቁን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ቀጣይ እርምጃዎቹ ተጠባቂ ሆነዋል።

ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን የሥራ አስፈፃሚ አባላት በፅህፈት ቤት ተገኝተው ከቀኑ 5፡00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ሁኔታ እና ቀጣይ አሰልጣኝ ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡ በተለይም አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ወይንስ አዲስ አሰልጣኝ ይቀጠራል የሚሉ ጉዳዮች ሁለት ሰዓታት እንደሚፈጅ በሚጠበቀው ስብሰባ ላይ አቅጣጫ እንደሚሰጥበት ይጠበቃል።

ሌላው በስብሰባው ይነሳል ተብሎ የሚጠበቀው ጉዳይ ውድድሮችን በድጋሚ ማስጀመር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንደሆነም ሰምተናል፡፡ በተለይ በቅርቡ የጤና ሚኒስቴር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመጠናቀቁ እና ሁሉም ከጥንቃቄ ጋር ወደየሥራ መስኩ መሰራማራት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ መመርያ በመሰጠቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በጉዳዩ ዙርያ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁንን አናግረን ስበሰባው እንደሚኖር ከመግለፅ ውጪ ስለ አጀንዳዎቹ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

error: