ሪፖርት| ነጌሌ አርሲ እና አዳማ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል

ሪፖርት| ነጌሌ አርሲ እና አዳማ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረጉ ጨዋታዎች ነጌሌ አርሲዎች ድሬዳዋ ከተማን 3-0 ሲያሸንፉ፤ አዳማ ከተማዎች በቢንያም አይተን ብቸኛ ግብ ምድረ ገነት ሽረን አሸንፈዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ነጌሌ አርሲ

ተመሳሳይ ነጥብ በመሰብሰብ በግብ ልዩነት ብቻ ተበላልጠው ጨዋታቸውን የጀመሩት ቡድኖቹ በጅማሮው ላይ ሁለቱም በፈጣን ሽግግሮች በተደጋጋሚ ሳጥን ጋር መድረስ ቢችሉም ግብ በማስቆጠሩ ረገድ ግን ነጌሌ አርሲዎች ቀዳሚ ነበሩ። 10ኛው ደቂቃ ላይ ከቤ ብዙነህ መነሻውን ከአማካይ ክፍል ያደረገ ተሻጋሪ ኳስ አግኝቶ በጥሩ ሁኔታ ወደ ሳጥን አሻግሮት ሀቢብ ከማል በግንባሩ ገጭቶ ያስቆጠረው ግብም ሰጎኖቹን መሪ ማድረግ ችሏል። በአጋማሹ ሁለቱም ቡድኖች ሳጥን በመድረስ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም ለግብ የቀረበ ሙከራ በማድረግ ረገድ ግን ነገሌ አርሲዎች የተሻሉ ነበሩ። 24ኛው ደቂቃ ላይ ከቤ ብዙነህ ከግራው የሜዳ ክፍል ገፍቶ ወደ ሳጥን በመግባት አክርሮ መቷት ግብጠባቂው አብዩ ካሳዬ የመለሳት ኳስም ተጠቃሽ ናት።

ከዕረፍት መልስ ተሻሽለው የቀረቡት ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስም ጫናዎችን መፍጠር ችለዋል። አቤል ነጋሽ 50ኛው ደቂቃ ላይ ከአስራት ቱንጆ የተሰነጠቀችለትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት በግቡ ቋሚ ለጥቂት የወጣችው እንዲሁም አቤል ነጋሽ በተመሳሳይ ከያሬድ ታደሰ የተቀበላትን ኳስ ወደ ግብ መቷት በግብ ጠባቂው ጥረት ግብ ከመሆን የተረፈችው ሙከራም ተጠቃሽ ናቸው።

በአጋማሹ በአመዛኙ መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው የተጫወቱት ነጌሌ አርሲዎች 78ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። አሸብር ውሮ ከራሱ የሜዳ ክልል አሻግሯት ተቀይሮ የገባው ናትናኤል ሰለሞን በመልሶ ማጥቃት ሂደት በጥሩ አጨራረስ ከመረቡ ጋር ያዋሀዳት ኳስም ለቡድኑ እፎይታ መስጠት የቻለች ግብ ነበረች። መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ላይም ሌላኛው ተቀይሮ የገባው አለኝታ ማርቆስ የድሬዳዋ ተጫዋቾች በራሳቸው የግብ ክልል የሰሩትን ስህተት ተከትሎ ያገኛት ኳስ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት ከፍ ማድረግ ችሏል። ሰጎኖቹም ጨዋታውን 3 – 0 በማሸነፍ ደረጃቸውን ከፍ ማድረግ ችለዋል።


ምድረ ገነት ኧረ ከ አዳማ ከተማ

ተመጣጣኝ የሚባል የኳስ ቁጥጥር ድርሻ
የታየበት የመጀመርያው አጋማሽ ቀዝቃዛ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተደረገበት ነበር። በአጋማሹ አዳማ ከተማዎች ኳስን ከሜዳቸው በመመስረት በሂደት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ፤ ሽረ ምድረ ገነቶች ደግሞ የመስመር አጥቂዎችን ኢላማ ባደረገ እንቅስቃሴ ለማጥቃት ጥረት ቢያደርጉም በሁለቱም በኩል ይሄ ነው የሚባል የግብ ሙከራን ሳንመለከት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ አዳማ ከተማዎች ራሳቸውን አሻሽለው የቀረቡበት ነበር። ጅማሮው ላይም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻሉ ሲሆን 57ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም አይተን አሻግሯት አህመድ ሁሴን በግንባሩ ገጭቶ የሞከራት ኳስም በግቡ ቋሚ ለጥቂት ወጥታለች። በአጋማሹ ጫናዎችን ፈጥረው መጫወት የቀጠሉት አዳማ ከተማዎች ብልጫቸው ፍሬ ያፈራበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል፡፡ በ85ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ በፈጣን መንገድ ካስጀመራት በኋላ አቡበከር ሳኒ አግኝቶ በጥሩ መንገድ የሰነጠቃት ኳስ ቢንያም አይተን መሬት ለመሬት በመምታት ከመረብ ጋር ያገናኛት ኳስም የማታ ማታ አዳማ ከተማን ባለ ድል ማድረግ ችላለች።