ሪፖርት | ቡናማዎቹ መቻልን በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሰዋል

ሪፖርት | ቡናማዎቹ መቻልን በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሰዋል

በሙከራዎች የታጀበ ማራኪ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ የዲቫይን ዋቹኩዋ ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ ቡናን ባለ ድል አድርጋለች።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው የዕለቱ ብቸኛ መርሐግብር በመጀመርያው አጋማሽ ተመጣጣኝ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የታየበት ቢሆንም በማጥቃቱ ረገድ ግን መቻሎች የተሻለ ብልጫ ነበራቸው።

መቻሎች የተሻለ ብልጫ በወሰዱበት እስከ አጋማሹ አካፋይ ድረስ በነበሩ ደቂቃዎችም በሁለት አጋጣሚዎች መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በረከት ደስታ ከማዕዝን አሻምቷት ፈቱዲን ጀማል በግምባሩ ከገጫት በኋላ ናትናኤል ፍሬው ከመስመር የመለሳት ኳስ እንዲሁም በተመሳሳይ በረከት ደስታ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ከቆመ ኳስ አሻምቷት ብሩክ ማርቆስ በግንባሩ ገጭቷት ፉዐድ ኢብራሂም ከመስመር ግብ ከመሆን ያዳናት ኳስ ደግሞ መቻልን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ወርቃማ  አጋጣሚዎች ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪም በረከት ደስታ በረዥሙ ተሻግራ መሐመድ አበራ በግምባሩ የጨረፋት ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራም ተጠቃሽ ናት።

ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች የግብ ዕድሎችን ሳይፈጥሩ የቆዩት ኢትዮጵያ ቡናዎችም በ34′ ደቂቃ ላይ ዲቫይን ዋቹክዋ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መቷት የግቡ አግዳሚ በመለሳት እጅግ ለግብ የቀረበች ሙከራ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ከሙከራው ከአስር ደቂቃ በኋላም ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል፤ አቡበከር አዳሙ በፈቱዲን ጀማል የቅብብል ስህተት ኦካይ ጁል ያቋረጣትን ኳስ አግኝቶ በመልሶ ማጥቃት በድንቅ ክህሎት ወደ ሳጥን ከገባ በኋላ ነፃ ለነበረው ዲቫይን ዋቹኩዋ አቀብሎት አማካዩ ከመረቡ ጋር ያዋሃዳት ኳስም ቡናማዎቹን መሪ ማድረግ ችላለች።

እጅግ ማራኪ ፉክክር የተደረገበት ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ባደረጓቸው ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች የታጀበ ነበር።

በአጋማሹ በፍቃዱ ዓለማየሁ በሁለት አጋጣሚዎች ያደረጋቸው ሙከራዎችም የቡናዎችን መሪነት ከፍ ለማድረግ የተቃረቡ ነበሩ፤ በተለይም ከሳጥኑ ቀኝ ክፍል ካደረጋት ሙከራ በኋላ በመልሶ ማጥቃት ሂደት ተገኝታ ዮርዳኖስ ሲሳይ ያመቻቻትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት የግቡን ቋሚ የመለሳት ሙከራ ለግብ የቀረበች ነበረች።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጫና የፈጠሩት መቻሎችም የአቻነት ግብ ለማግኘት የተቃረቡባቸው ሁለት ወርቃማ አጋጣሚዎች ፈጥረዋል። ዓለምብርሃን ይግዛው አሻምቷት ቸርነት ጉግሳ በግንባሩ ከገጫት በኋላ ግብ ጠባቂው እንዳሻው እሸቴ በድንቅ ብቃት የመለሳት ኳስ እንዲሁም አብዱልከሪም ወርቁ ከግቡ ቅርብ ርቀት መቷት  ፉዓድ ኢብራሂም እንደምንም ያወጣት ኳስም ጦሩን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ናቸው። ጥሩ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታም ኢትዮጵያ ቡና በዲቫይን ዋቹኩዋ ብቸኛ ግብ ባለ ድል ሆኗል።