ሪፖርት| ሐይቆቹ ወደ መሪው የተጠጉበት ድል ሲቀዳጁ ወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት| ሐይቆቹ ወደ መሪው የተጠጉበት ድል ሲቀዳጁ ወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሀዋሳ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ
የወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ 1 ለ 1 ተጠናቀቀ

 

 

ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

 

በአዳማ በተካሄደው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የተሻለ ኳስ ቁጥጥር ድርሻ እንዲሁም የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ብልጫ የወሰዱበት ነበር። በተለይም ሀሰን ሁሴንን ዒላማ ባደረጉ ኳሶች የሐይቆቹን የተከላካይ ክፍል የፈተኑት ኤሌክትሪኮች
ሀሰን ሁሴን በግንባሩ ገጭቶት ሰይድ ሀብታሙ ባዳነው እንዲሁም አቤል ሀብታሙ በአንድ ለአንድ ግኑኘነት ወንድማገኝ ተሾመን በማለፍ መቶት ሰይድ ሀብታሙ ሳይጠበቅ በተቆጣጠረው ሙከራዎች ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል።

ሐይቆቹም ምንም እንኳን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል፤ በረከት ሳሙኤል ከመስመር የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ገጭቶት ግብ ጠባቂው ያዳነበት እንዲሁም ምንተስኖት ቶማስ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ እና ጌታነህ ከበደ ሳጥን ውስጥ በደረቱ አብርዶ ያደረገውን ሙከራም ተጠቃሾች ናቸው።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ አጋማሹን የጀመሩት ሐይቆቹ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው ተጫዋች አማካኝነት ግብ አግኝተዋል። ተቀይሮ የገባው ተባረክ ሄፋሞ 48ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ ከማዕዘን ያሻገራትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከመጀመሪያ አጋማሽ አንፃር ደካማ እንቅስቃሴ ያደረጉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ወደ ፊት ሄደው የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። የጨዋታ መጠናቀቂያ የዕለቱ ዋና ዳኛ ተፈሪ አለባቸው ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ፍፁም ቅጣት ምት ከሰጡ በኋላ በረዳቶቻቸው ድጋፍ ውሳኔውን የሻሩበት አጋጣሚም የአጋማሹ ትኩረት ሳቢ ጉዳይ ነበር። ጨዋታው ሊጠናቀው ደቂቃዎች ሲቀሩትም ጌታነህ ከበደ ከመዓዝን ምት በቀጥታ ባስቆጠራት ግብ ሀዋሳ ከተማዎች ጨዋታውን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

 

ወላይታ ድቻ ከ አዳማ ከተማ

ምሽት ወላይታ ድቻ ከአዳማ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ወላይታ ድቻ በማጥቃቱ ረገድ አዳማ ከተማ ደግሞ በኳስ ቁጥጥሩ በኩል ብልጫ የወሰዱበት ነበር።

የጠራ የግብ ሙከራ ለመመልከት ዘለግ ያሉ ደቂቃዎች በፈጀው ጨዋታ አዳማዎች ቢኒያም አይተን በአንድ ለአንድ ቅብብል ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ ባደረጋት እና ቢኒያም ገነቱ ባዳነበት ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ከደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ወላይታ ድቻዎች መሪ የሆኑበት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ዮናታን ኤልያስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቷት ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ በአግባቡ ያልተቆጣጠራት ኳስ በቅርብ ርቀት የነበረው ቴዎድሮስ ሀይለማርያም በቀላል ንክኪ ወደ ግብነት ቀይሮ የጦና ንቦቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

አዳማ ከተማዎች ግብ ካስተናገዱ በኋላ ሀይደር ሸረፋ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ባደረጋት ሙከራ አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረግ ቢችሉም አጋማቹ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት 1 ለ 0 ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ የጨዋታ ብልጫም ሆነ በማጥቃት እንቅስቃሴ ረገድ ተሻሽለው የተመለሱት አዳማ ከተማዎች ከተደጋጋሚ ጥረት በኋላ 69ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረው አቻ መሆን ችለዋል። ሳሙኤል የሃንስ ከግራ መስመር አሻግሯት አቤኔዘር ሲሳይ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም አዳማዎችን ወደ ጨዋታ የመለሰች ግብ ነች።

የጦና ንቦቹም ግብ ካስተናገዱ በኋላ በ77 ኛው ደቂቃ ላይ በቅዱስ ቂርቆስ አማካኝነት አስቆጪ የግብ ሙከራ ማድረግ ሲችሉ አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው 83ኛው ደቂቃ ላይም ሀይደር ሸረፋ ከቆመ ኳስ አሻግሯት ቢኒያም ገነቱ በአግባቡ ያልተቆጣጠራት ኳስ ተጠቅሞ አብዱልፈታህ ሰፋ ያደረጋት እና ቢኒያም ገነቱ ከመስመሩ ባዳናት ኳስ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታም በሁለቱም አጋማሾች በተቆጠሩ ግቦች 1ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።