18ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ አራት ተጠባቂ ጨዋታዎች የሚጠናቀቅ ሲሆን ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እነሆ !

ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ አርባምንጭ ከተማ
ከተከታታይ 5 አቻዎች በኋላ ሀዲያ ሆሳዕናን 2ለ1 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን ሦስተኛ ድል ያሳኩት ወልዋሎዎች ለሁለተኛ ጊዜ ሁለት ጎሎችን ባስቆጠሩበት በዚህ ጨዋታ ተሻሽለው የቀረቡበት መንገድ ትኩረትን የሚስብ ነው። በሙሉ ደቂቃዎች ዕረፍት የለሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ይዘው የቀረቡት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ ዕውቅናን ያገኙ ሲሆን ይህንን የጨዋታ መንገድ አስቀጥለው ተከታታይ ድሎችን በማሳካት ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ዛሬ ከአዞዎቹ ጋር ጠንካራ ፍልሚያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በውድድር ዓመቱ ድል ያላሳካው ብቸኛ ቡድን አርባምንጭ ከተማ በታሪኩ እጅግ አስከፊውን የሊግ ቆይታ እያደረገ ይገኛል። ካደረጋቸው 17 ጨዋታዎች በሰባቱ አቻ ተለያይቶ በ10 ጨዋታዎች የተሸነፈው ቡድኑ በተለይም 7 አስቆጥሮ 20 ግቦች ማስተናገዱ ሁኔታውን ይገልጻል። በአማካይ በሁለት ጨዋታ አንድ ጎል እንኳ ማስቆጠር ያልቻለውን የፊት መስመር እና በአማካይ በጨዋታ ሁለት ግብ የሚቆጠርበትን የመከላከል አደረጃጀት ለማሻሻል በአዲስ የተሾሙት አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ይህንን ኃላፊነት በምን መንገድ ይወጡታል የሚለው ትኩረትን የሚስብ ነው።
ወልዋሎዎች ሰመረ ሀፍታይ እና ብሩክ እንዳለን በቅጣት፤ ኮንኮኒ ሃፊዝ እና ስምዖን ማሩን ደግሞ በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም። ያሬድ ከበደ ግን ከጉዳት አገግሟል። በአርባምንጭ ከተማ በኩል ሳሙኤል አስፈሪ በጉዳት ብሩክ ባይሳ እና አንበሉ ይሁን እንዳሻው በቅጣት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች 4 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈው በሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ወልዋሎ 5 አርባምንጭ ከተማ 4 ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል።
መቐለ 70 እንደርታ ከ ኢትዮጵያ ቡና
አሰልጣኝ ፀጋይ ኪዳነማርያምን ከቀጠሩ በኋላ ባደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች ሦስት አሸንፈው በአራት አቻ የተለያዩት ምዓም አናብስት በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛሉ። በተጠቀሱት ሳምንታት ሁለት ግቦች ብቻ የተቆጠሩበት ጠንካራ የተከላካይ መስመር የገነቡት አሰልጣኙ በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል ግን ስድስት ግቦችን ማስቆጠራቸው ተከታታይ ድሎችን ለማሳካት ማሻሻል እንዳለባቸው የሚጠቁም ነው። በዛሬው ጨዋታም ድልን ከተራበው ኢትዮጵያ ቡና ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ አሸንፈው ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይገመታል።
አሰልጣኝ ሳምሶን አየለን ከቀጠሩ እና አሰልጣኙ ቴክኒካል ቦታ ላይ ቡድኑን መምራት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ፋሲል ከነማን 2ለ0 ባሸነፉበት እና ከሀዋሳ ጋር 1ለ1 በተለያዩበት ጨዋታ ማራኪ ቅንጅት አሳይተው የነበሩት ቡናማዎቹ በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ግን በሲዳማ እና በንግድ ባንክ ሽንፈት አስተናግደዋል። ውጤቱ በተደጋጋሚ ጨዋታዎች እንደተመለከትነው ከአማካይ ስፍራ ተጫዋቾቹ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው በሚታየው ቡድን ውስጥ በእነዚህ ሁለቱ ጨዋታዎች ግቦችን ላለማስቆጠራቸው ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመግባት መቸገራቸው ዋነኛ ምክንያት ነው። ሆኖም ዛሬ በመቐለ የሚሸነፉ ከሆነ ወደ ወራጅ ቀጠናው የሚገቡ ሲሆን ከዚህ አስከፊ ሁኔታ ለመላቀቅ ድልን አብዝተው በማለም ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 6 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 2 መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ 1 ጨዋታ ማሸነፍ ችለዋል፤ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ በነጥብ መጋራት የተጠናቀቁ ናቸው። በግንኙነቱ ቡናማዎቹ 6፣ ምዓም አናብስት 3 አስቆጥረዋል። (በ2012 በኮቪድ ምክንያት የተሰረዘውና 1-1 የተጠናቀቀው ጨዋታን አያካትትም)
ፋሲል ከነማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ከሦስት ሳምንታት በኋላ አርባምንጭን 3ለ2 በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱት ዐፄዎቹ እንደ ድሉ ሁሉ ወደ ግብ ማስቆጠር የተመለሱትም ከእነዚሁ ሳምንታት በኋላ ነበር። ለተመልካች ሳቢ በነበረው የአርባምንጩ ጨዋታ ከፍ ባለ ተነሳሽነት ቀርቦ ወሳኝ ድል ያሳካው ቡድኑ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ከመሪው ሲዳማ ቡና በ5 ነጥቦች ርቀት 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ትናንት ሲዳማ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ይህንን ጨዋታ አሸንፎ የነጥብ ልዩነቱን ወደ ሁለት ለማጥበብ የሚችልበት ትልቅ አጋጣሚ አግኝቷል። ሆኖም በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ እንደሚደረግ በሚጠበቀው በሳምንቱ ትልቅ ጨዋታ ድል ለማድረግ እንዳለፈው ሳምንት ሁሉ የአጥቂ መስመራቸውን ውጤታማነት ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ድሬዳዋን 4ለ0 ካሸነፉ በኋላ በመቻል 2ለ0 ተሸንፈው ከሽረ ምድረገነት ጋር ያለ ግብ የተለያዩት ጊዮርጊሶች በ23 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ባሳለፍነው ሳምንት እንደጠቀስነው ዝግ ያለ አጀማመር በማድረግ የሚታወቁት ፈረሰኞቹ በሽረው ጨዋታም በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ከፍተኛ ብልጫ ቢኖራቸውም አጨቃጫቂ በሆነ ሁኔታ ከተሻረው የመጨረሻ ደቂቃ የፍጹም ጥላሁን ግብ ውጪ የነበራቸው አባካኝነት መስተካከል የሚገባው ነው። ተጋጣሚያቸው ፋሲል ከነማ 7 ግቦች ( አንድ ግብ ለማስተናገድ ከሁለት በላይ ጨዋታዎች የሚጠብቅ ) ብቻ የተቆጠሩበት ቡድን ከመሆኑ አንጻር የሚፈጠሩ የግብ ዕድሎችን አለመጠቀም ዋጋ ሊያስከፍላቸው ይችላል። በአንጻሩ ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ በተሻለ መነሳሳት ላይ ያለውን የዐፄዎቹ የማጥቃት ኃይል ለማቆምም አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ምን መላ ይዘይዳሉ የሚለው ተጠባቂ ነው።
በፋሲል ከነማ በኩል ጉዳት ላይ የነበሩት በረከት ግዛው እና አብዱልአዚዝ አማን ወደ ሜዳ የተመለሱ ሲሆን አምሳሉ ጥላሁን በጉዳት እንዲሁም አቤነዘር ዮሐንስ በቅጣት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ሀብታሙ ጉልላት በቅጣት ምክንያት አይኖርም።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በፕሪሚየር ሊጉ ለ17 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን 40 ግቦች በተቆጠሩበት ግንኙነታቸው 17 ግቦችን ያስቆጠረው ፋሲል ከነማ ለ8፤ 23 ግቦችን ያስቆጠረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ለ7 ጊዜያት ድል ሲቀናቸው ሁለቱ ጨዋታዎች በአቻ ተጠናቀዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 2000 ዓ/ም ላይ የ 2-0 ፋሲል ከነማ ደግሞ 2011 ዓ/ም ላይ የ 3-0 የፎርፌ ውጤት አግኝተዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ነጌሌ አርሲ
ከሁለት የአቻ እና ከሁለት የሽንፈት ውጤቶች በኋላ በመጨረሻው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ላይ ድል የተቀዳጀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 20 ነጥቦችን ሰብስቦ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ከሲዳማ (24) እና መቻል (23) ቀጥሎ ከፍተኛውን የግብ መጠን (20) ያስቆጠረው ንግድ ባንክ በአንጻሩ ከ17 ጨዋታዎች በአሥራ ሦስቱ ጨዋታዎች በድምሩ 20 ግቦችን ማስተናገዱ በጉዞው ላይ እንቅፋት እየሆነበት ይገኛል። በጠንካራ የማጥቃት ሽግግር ከሚታወቁ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው የአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ቡድን በዛሬው ጨዋታ ድል የሚያደርግ ከሆነ እንደ ሚያስቆጥረው ግብ ልዩነት እስከ አራት ደረጃዎችን ማሻሻል የሚችል ይሆናል። ሆኖም ግን ደካማ የመከላከል አደረጃጀታቸው በካቤ ብዙነህ የሚመራውን የነጌሌ አርሲ የማጥቃት ኃይል የመመከት ብቃቱ ከጨዋታው በፊት ጥርጣሬን የሚያጭር ነው።
ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ተጋርተው በሀዋሳ ከተማ የተሸነፉት ነጌሌ አርሲዎች በመጨረሻው ሳምንት ግን የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን አሸንፈው በተሻለ የራስ መተማመን ለዛሬው ጨዋታ ይቀርባሉ። በ29 ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሰጎኖቹ ይህንን ጨዋታ አሸንፈው ከመሪው ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት አጥብበው ጫና ለማሳደር እያለሙ ንግድ ባንክን ይገጥማሉ። በወቅታዊ ብቃት የሊጉን ምርጥ ተጫዋች ካቤ ብዙነህን የያዘው ቡድኑ ይህ ተጫዋች በተጋጣሚ ቡድን ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ከመግባቱ አንጻር ሌሎች ተጨማሪ የማጥቂያ መንገዶችን መፈለግ ደግሞ የአሰልጣኝ ቱሉ ደስታ የቤት ሥራ ነው።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካሌብ አማንክዋህን በቅጣት ምክንያት የማያገኝ ሲሆን ነገሌ አርሲዎች ጉዳት ላይ ካለው አብዱልባሲጥ ከማል በተጨማሪ ቦና ቦካን በቅጣት ምክንያት አያገኙም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ የመጀመሪያ የእርስበርስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

