በ25ኛው ሳምንት የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ እና ፋሲል ከነማ እንዲሁም መቻል እና ምድረ ገነት ሽረ ነጥብ ተጋርተዋል

ድሬዳዋ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ
በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ጅማሮውን ሲያደርግ 9:00 ላይ ድሬዳዋ ከተማን ከ ፋሲል ከነማ አገናኝቷል። ጨዋታውም በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ድሬዳዋ ከተማዎች የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም ነገር ግን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግብ ለማስቆጠር ተቸግረው ተስተውለዋል። በአጋማሹም ይሄ ነው የሚባል የግብ አጋጣሚዎችን ሳያስመለክቱን ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ፋሲል ከነማዎች የተጫዋቾች ለውጦችን በማድረግ የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ደርሰው ጥራት ያላቸውን የግብ እድሎችን በመፍጠር ረገድ ውስንነት ታይቶባቸዋል። በተመሳሳይ ድሬዳዋ ከተማዎች እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው ያለ ግብ 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
መቻል ከ ምድረ ገነት ሽረ
በሙከራ በታጀበው እና መቻሎች ብልጫ በወሰዱበት በመጀመሪያው አጋማሽ ገና በ6ኛው ደቂቃ ላይ ኢላማውን ባልጠበቀው የግሩም ሀጎስ የግንባር ኳስ ሙከራ እንዲሁም በ12 ተኛው ደቂቃ ላይ በኮሊንስ ኮፊ ከሳጥን ውጭ በተመታ ኳስ ግብ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ መልሶባቸዋል።
ጫናዎችን ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት መቻሎች 22ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ ራሱ ይዞ በመግባት ከሳጥኑ ውጭ የመታውን ኳስ እንዲሁም 23ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ግሩም ሀጎስ አክርሮ በመምታት ቢሞክርም በአጋማሹ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ በጥሩ ቅልጥፍና ግብ ከመሆን ታድጓቸዋል።

ከዕረፍት መልስ 50ኛው ደቂቃ ላይ መቻሎች የልፋታቸውን ዋጋ ያገኙበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። መነሻውን ከቀኝ መስመር አድርጎ የተሻማውን እና ብሩክ ማርቆስ በግንባሩ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ዓለምብርሃን ይግዛው ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
የተጫዋች ለውጥ በማድረግ የአቻነት ግባቸውን ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸውን የቀጠሉት ምድረ ገነት ሸረዎች 77ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት ተካልኝ ደጀኔ በቀጥታ ግሩም በሆነ መንገድ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን አቻ አድርጓል። ጨዋታውም ጥሩ ፉክክር አስመልክቶ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።


