የሸገር ከተማው ተስፈኛው አጥቂ ዳዊት ካሳው ከቤልጂየም ክለብ የሙከራ ዕድል አግኝቷል።

ከቅርብ ጊዜያት ወደህ ከተመለከትናቸው ተስፈኛ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው እና የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከ22 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ መድረክ ስትመለስ ሰባት ጎሎችን በማስቆጠር ራሱን ከስፖርት ቤተሰቡ ጋር ያስተዋወቀው ዳዊት ካሳው የቤልጂየም ጁፕሊየር ፕሮ ሊግ ክለብ ለሙከራ እንደፈለገው አውቀናል።
መረጃውን ያደረሰን Nordic Sky Agency, (ኖርዲክ ስካይ ኤጀንሲ) እንደነገረን ከሆነ ለጊዜው የክለቡን ስም ለመጠቅስ እንደሚቆጠቡ ይህም የሆነው የቪዛ ሂደቱን እና የሸገር ከነማ ፈቃድ በመጠባበቅ ላይ በመሆናቸውን እንደሆነ ጠቅሰው ሁኔታዎች ሲጠናቀቁ የሚሄድበትን ክለብ እና ቀጣይ ሂደቶችን ለሶከር ኢትዮጵያ አስቀድመው መረጃውን እንደሚያጋሩ ጠቁመዋል።
ከውቢቷ ባህር ዳር ከተማ ፕሮጀክት የእግር ኳስ መነሻውን ያደረገው ዳዊት በስሪ ፖይንት አካዳሚ ቆይታ በኋላ ለኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እና በሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን የሚሳተፈው ሸገር ከተማ ተጫዋች መሆኑ ይታወቃል።

