ወልዋሎ አህጉራዊውን ጨዋታ የተመለከተ መግለጫ አውጥቷል

በካፍ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ እየተሳተፈ የሚገኘው እና በመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ሂላል አል ሳህልን በማሸነፍ በሁለተኛው ዙር ከሊብያው አል አህሊ ፕሪፖሊ ጋር የሚጫወተው ወልዋሎ የሜዳውን ጨዋታ በሊብያ ለማድረግ እንደወሰነ ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል።
የመጀመሪያው ጨዋታ በድሬዳዋ ስታዲየም ለማድረግ አስመዝግቦ የነበረው ክለቡ ለዓዲግራት ከተማ አስተዳደር እና ለዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የበጀት ጥያቄ አቅርቦ ቀደም ሲል ተጋጣሚው ያቀረበውን መሰል ጥያቄ ውድቅ አድርጎ እንደነበር ጠቅሶ በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ይህ ነው የሚባል በጀት ማግኘት ባለመቻሉ የሊብያው ክለብ አል አህሊ ትሪፖሊ ያቀረበው ውል ለመቀበል እንደተገደደ ገልጿል።
ክለቡ በመግለጫው ላይ በቅርብ ዓመታት በበጀት እጥረት ምክንያት ካጋጠሙት ችግሮች ለመላቀቅ ይህንን ውሳኔ እንደወሰነ ጠቅሶ ውሉ ጠቀም ያለ ክፍያ፤ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት መብት ገቢ እና የስታዲየም ገቢ የሚያስገኝለት መሆኑና በተጨማሪም ተጋጣሚው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ክለቡን ለመደገፍ የሚያስችለውን ስምምነት እንደፈፀመ ገልጿል።
ከዚህ ቀደም ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ኢትዮጵያ መድን የግብፆቹ አል አህሊ እና ፒራሚድ ባቀረቡላቸው ተመሳሳይ ጥያቄ አህጉራዊ ጨዋታዎቻቸውን በግብፅ ማድረጋቸው ይታወሳል።

