ፕሪምየር ሊግ ትኩረት | መላ ሊበጅለት የሚገባው የሜዳ ጠርዝ ማስታወቂያዎች ጉዳይ

ፕሪምየር ሊግ ትኩረት | መላ ሊበጅለት የሚገባው የሜዳ ጠርዝ ማስታወቂያዎች ጉዳይ

የዚህኛው ሳምንት ሌላኛው የትኩረት አጀንዳችን ዝብርቅርቅ ያለው የሜዳ ጠርዝ ማስታወቂያዎች ጉዳይ ነው።

በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ከተመለከትናቸው ጉዳዮች መካከል በሜዳ ጠርዝ የሚቀመጡ በመጠን የተለያዩ ማስታወቂያዎች ጉዳይ አንዱ ነው ፤ ይህም ለዕይታ ከመረበሹ ባለፈ የሊጉን ደረጃ ፍፁም የሚያወርድ ሆኖ አግኝተነዋል።

እርግጥ በሜዳ ጠርዝ የሚቀመጡ ዲጂታል የማስታወቂያ ቦርዶች ለመሰል ክፍተቶች ምላሽ ቢኖራቸውም በሊጋችን ነባራዊ ሁኔታ እነዚህን ማግኘት ባለመቻሉ ታትመው በብረት መዋቅር ላይ የሚለጠፉት ማስታወቂያዎች መጠን ላይ ወጥ አሰራርን መከተል ይገባል።

ችግሩ በሁሉም ስታዲየሞች የወል ችግር የነበረ ቢሆንም ሸገር ከተማን ከኢትዮጵያ ቡና ያገናኘው ጨዋታ የሜዳ ጠርዝ ማስታወቂያዎች ጉዳይ መፍትሄ ስለመሻቱ አይነተኛ ማሳያ ነበር ፤ በተለያየ መጠንና አቀማመጥ የተደረደሩት የተለያዩ ማስታወቂያዎችን በሜዳው ጠርዝ በስፋት ያስለዋልንበት ጨዋታ ነበር።

ሌላው ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ማስታወቂያ ቦርዶቹ መዋቅር የሚሰሩበት ቁስና ከሜዳው ምን ያህል መራቅ አለባቸው የሚለው ጉዳይ ነው ፤ ካፍን ጨምሮ ሌሎች ኮንፌደሬሽኖች በብረት የሚሰሩ የማስታወቂያ መዋቅሮች ከተጫዋቾች ደህንነት አንፃር አደጋን ይደቅናሉ በሚል ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የከለከሉ ሲሆን በምትኩም ከእንጨት ውጤት የሚሰሩ ግብዓቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያዛል።

ሌላኛው በተለይ ማስታወቂያዎች ከሜዳው የመጨረሻ መስመር በቅርብ ርቀት የመቀመጣቸው ጉዳይ ነው ይህም በሜዳው ጠርዝ ንክኪ ያጋጠማቸው ተጫዋቾች ሆነ ፍጥነታቸውን መቆጣጠር ያልቻሉ ተጫዋቾች ከማስታወቂያ ቦርዶቹ ጋር ሲላተሙ አለፍ ሲል ማዕዘን ምቶችን ለማሻማት ሲቸገሩ እንዲሁ አስተውለናል ይህም ጉዳይ ተጫዋቾችን ለአደጋ ሊዳርጉ የሚችልበት ዕድል ሰፊ መሆኑም እንዲሁ ልብ ሊባል ይገባል።

እንደ ሊግ ሊጋችን ለማሳደግ ከተፈለገ ለእያንዳንዱ ጉዳዮች ትኩረት መስጠት የግድ ይላል ፤ በጉዳዮቹም ዙርያ አስገዳጅ መመርያዎችን ተግባራዊ ማድረግ የሊጉን ደረጃ ለማሻሻይ አይነተኛ ሚናን ከመወጣቱ ባለፈ ለተጫዋቾች ደህንነትም ከሚኖረው አበርክቶ አንፃር አወዳዳሪው አካል ልብ ሊለው ይገባል።