የዚህኛው ሳምንት ቀዳሚው ትኩረታችን የሚሆነው በድርጊቶች የተሞላው 53ኛው የሸገር ደርቢ ነው!
የሸገር ደርቢ የደጋፊዎች ድባብ እንጂ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው አመርቂ አይደለም የሚለው አባባል ለዘመናት የዚህ ታላቅ ደርቢ መገለጫ ነበር ፤ እርግጥ በቅርብ ዓመታት ተደጋጋሚ የአቻ ውጤቶችና ደካማ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች የጨዋታው መገለጫ የነበሩ ቢሆንም 53ኛው የሸገር ደርቢ ግን እውነተኛ የደርቢ ጣዕምን ያጣጣምንበት ነበር።
ከጨዋታው ቀናት አስቀድሞ አብዛኛው የስታዲየም መግቢያ ትኬቶች ተጠናቀው ባለቁበት በዚሁ ጨዋታ ከጨዋታው ጅማሮ ሰዓታት አስቀድሞ በአዲስ አበባ ስታዲየም ዙርያ የነበረው የደጋፊዎች ድባብ ፍፁም ልዩ ነበር ፤ ሜዳ ላይም በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ የመጨረሻ 20 ደቂቃዎች የተመለከትነው ትንቅንቅ የሁለቱን ክለብ ደጋፊዎች ይቅርና ገለልተኛ የእግር ኳስ ተመልካችን ሁሉ ልብን ሰቅዞ የሚይዝ አጋጣሚ ነበር።
3 ጎሎችንና 3 ቀይ ካርዶችን በተመለከትንባቸው እነዚህ 20 ደቂቃዎች በስታዲየሙ የነበረው ስሜት ልዩ ነበር ፤ በተለይ ኢትዮጵያ ቡናዎች በበፍቃዱ ዓለማየሁና ኦካይ ጁል አማካኝነት 2-0 ከመሩ በኋላ በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት አማኑኤል ኤርቦ ፈረሰኞቹን ወደ ጨዋታ የመለሰችዋን ግብ ካስቆጠሩ በኋላ የነበረው ሂደት አስደናቂ ነበር ፤ ቡናማዎች መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ፈረሰኞቹ ደግሞ እንየው ስለሺንና አሚር ሚስባህን ቀይረው በማስገባት በጀብደኝነት በአራት አጥቂ ለመጫወት ጥረት ያደረጉባቸው ደቂቃዎች ተመልካቹን ቁጭ ብድግ ያደረጉ ቅፅበቶች ነበሩ።

ከዚህ ባለፈ ምንም እንኳን በፍቃዱ ዓለማየሁና ፣ በረከት ወልደዮሀንስ በኢትዮጵያ ቡና በኩል እንዲሁም ያሬድ የማነ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በቀይ የወጡባቸው አጋጣሚዎች ተገቢ ባይሆኑም ለደርቢው ግለት ግን ሌላ ተጨማሪ አበርክቶ የነበራቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።
የደርቢ ጨዋታዎች ከከተማ ባላንጣነት ባሻገር ፍፁም ጥራታቸው የላቁ የሜዳ ላይ ፉክክሮች ፣ አልሸነፍ ባይነት ፣ የጋለ ስሜት ፣ አደገኛ ጥፋቶችና ካርዶች መለያቸው እንደመሆኑ 53ኛው ሸገር ደርቢ ይህን አሳይቶን አልፏል።
ከሁሉም በላይ በዚህ ልክ የጋለ ስሜት ከነበረው የሜዳ ላይ ፉክክር መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱም ክለቦች ደጋፊዎች ፍፁም ስፓርታዊ ጨዋነት በተሞላበት መንገድ ተጫዋቾቻቸውን ስለ ሜዳ ላይ ተጋድሏቸው አመስግነው በሰላም ወደ መጡበት የመመለሳቸው ጉዳይ ሊበረታታ የሚገባ ሲሆን ፤ መሰል ብርቱ የሜዳ ላይ ፉክክሮች እና ፍፁም ስፓርታዊ ጨዋነት የእግር ኳሳችን ባህል እንዲሆኑ እንመኛለን።

