ከዓምና በተሻለ ቁጥር የከተማውን ክለብ ለማየት ወደ ስታዲየም እየመጣ የሚገኘው የአዳማ ከተማ ደጋፊ ጉዳይ የዚህ ሳምንት የትኩረታችን አንደኛው ማዕከል ሆኗል።
የሀገራችን ከፍተኛው የሊግ እርከን ውድድር የሆነው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ያለፉትን ስድስት ዓመታት ከተከናወነበት መንገድ ለየት ባለ ቅርፅ እና መልክ እየተደረገ ይገኛል። ለሜዳ እና የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች የቀረበ የሆነው የዘንድሮ የውድድር ቅርፅ እግርኳሳዊ በሆኑ ምክንያቶች እጅግ በርካታ ጥቅሞችን ለሁሉም አካላት መስጠቱን ገና በአንደኛ እና ሁለተኛ ሳምንታት እየተመለከትን እንገኛለን። ይህ የውድድር ቅርፅ ካመጣቸው ትሩፋቶች ዋነኛው እና ቀዳሚው ክለቦች በመቀመጫ ከተማቸው ወይም በርከት ያሉ ደጋፊዎቻቸውን በሚያገኙበት አካባቢ የሜዳ ላይ ጨዋታቸውን ማድረጋቸውና የሜዳ ላይ ጥቅማቸውን ማግኘት መጀመራቸው እንደሆነ ቢታመንም በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ውድድር ግን ይህንን የሜዳ ላይ ጥቅም በውጤት ረገድ አንድም ክለብ ሳይጠቀምበት መውጣቱ የመጀመሪያ ሳምንት የትኩረታችን ማዕከል ሆኖ ማለፉ አይዘነጋም። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ክለቦች አሁንም የሜዳ ላይ ጥቅማቸውን የሚያገኙበት የደጋፊዎች ፊት የመጫወት ትሩፋት አሁንም እያደገ መጥቷል። የዛሬው ትኩረታችን ደግሞ ያለፉትን ዓመታት የከተማውን ክለብ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሊጉን ቡድኖች አስተናግዶ ውድድሮችን ሲያከናውን የነበረው የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም ባሳለፍነው ዓርብ የከተማው ክለብ አዳማ ከተማ ከሸገር ከተማ ጋር ጨዋታ ሲያደርግ ከወትሮ በተለየ በስታዲየሙ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ደጋፊዎች መታየታቸውን በተመለከተ ነው።
በርካታ የእግርኳስ ተጫዋቾችን ያፈራው እንዲሁም እግርኳስ በደንብ የሚወደድበት ከተማ የሆነው አዳማ ከኮቪድ በፊት የከተማው ክለብ በሊጉ ሲወዳደር ፖስታ ቤት አካባቢ በሚገኘው የድሮ ስታዲየም (አበበ ቢቂላ ስታዲየም) በርከት ያሉ ተመልካቾችን መመልከት ብርቅ አልነበረም። ታዲያ ይህ ድሮ በየጨዋታ ቀኑ በቀይ እና ጥቁር ቀለሞች ቡድኑን ሲደግፍ የነበረው ተመልካች የሊጉ ጨዋታዎቹ ወደ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ሲዞሩ እንዲሁም የውድድር ቅርፁ ሲለወጥ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጥቶ በተለይ ዓምና እጅግ በቁጥር ያነሰ ተመልካች ብቻ በስታዲየሙ መመልከት ልማድ ሆኖ ነበር። ለዚህ ዋነኞቹ ምክንያቶች ከላይ የገለፅነው የውድድሩ ቅርፅ ለተመልካች አታካች መሆኑ ብቻ ሳይሆን የስታዲየሙ ከመሐል የከተማው ክፍል ራቅ ማለቱ፣ የክለቡ ውጤታማነት እንዲሁም በስራ ቀናት ጭምር ጨዋታዎች መደረጋቸው ሲሆኑ አሁን ግን በሳምንት አልያም በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ ከተማው የሚያስተናግደውን የባለሜዳ ክለብ ጨዋታ በናፍቆት እንዲመለከት በር የከፈተ የውድድር ቅርፅ መመለሱ ተመልካቾችን ወደ ሜዳ እየመለሰ ይመስላል። በተለይ ደግሞ የጨዋታ ቀናት ከተለምዷዊ የስራ መደበኛ ቀናት እና ሰዓታት በተለየ መንገድ መደረጉ ለደጋፊዎች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። በዚህም አብዛኛው የከተማው ነዋሪ፣ ነጋዴና ወጣት ከዕለት ተዕለት የስራ ውጥረት ወጥቶ ለመዝናናት እና ከከተማው ማኅበረሰብ ጋር ስፖርታዊ ድባብ ለማሳለፍ አስችሎታል።

ከ2 ሺ የሚልቁ ተመልካቾች ወደ ስታዲየም እንደገቡ መረጃዎች ያመላክታሉ። እርግጥ ይህን ቁጥር በግርድፉ ስንመለከት ያነሰ ቢመስልም ዓምና አዳማ ከተማ በዚህ ሜዳ ጨዋታውን ሲያደርግ ሲመዘገቡ ከነበሩ ቁጥሮች አንፃር እድገቶች እንዳሉት መናገር ይቻላል።
ሶከር ኢትዮጵያ ከሚመለከታቸው አካላት በሰበሰበችው መረጃ አምና አዳማ ከተማ በሜዳው ጨዋታ ሲያደርግ በመቶዎች የሚቆጠሩ አልፎ አልፎ ብቻ አንድ ሺን በጥቂቱ የሚዘሉ የተመልካች ቁጥሮች እንደሚመዘገቡ አውቀናል። ዓምና በተመዘገበ መረጃ በስታዲየሙም አዳማ ጨዋታ ሲያደርግ ዝቅተኛው የተመልካች ቁጥር 32 ብቻ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል (ስታዲየም ትኬት ቆርጦ የገባው የተመልካች ቁጥር እንደሆነ ልብ ይላል)። በግርምት አፍን በእጅ የሚያሲዘው ይህ ዝቅተኛ የተመልካች ቁጥር ብቻ ሳይሆን አዳማ በሜዳው ሲጫወት የተመዘገበው ከፍተኛው የተመልካች ቁጥር 1,250 ብቻ መሆኑ ነው። ታዲያ ይህ ቁጥር ባለበት የዓርቡ ጨዋታ የተመልካች ቁጥር እድገት ሊበረታታ የሚገባው እንደሆነ ማንሳት ይቻላል። በተለይ ደግሞ በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራውና ጥሩ ስብስብ የያዘው ቡድኑ በሜዳ ላይ ብቃት በመልካም የውጤት ጎዳና የሚራመድ ከሆነ ከዚህም በላይ ተመልካቾች ወደ ስታዲየም እንደሚመጡና በሀላባ፣ ሆሳዕና እና አርባምንጭ እየተመለከትን ያለውን የደጋፊዎች ጎርፍ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ልንመለከት እንችላለን።

