ሀላባ ከተማ ባህር ዳር ከተማን ሲያሸንፍ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ነገሌ አርሲ እንዲሁም አዳማ ከተማ እና ሸገር ሲቲ ያለ ግብ ተለያዩ።
በዐቢዩ አረጋሽ

በሲቢኢ ኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪሚየር ሊግ የ2ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ሀላባ ከተማ በዮናታን ኃይሉ ብቸኛ ግብ ባህርዳር ከተማን 1ለ0 በማሸነፍ የሊጉን የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል። በሌሎች ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከነገሌ አርሲ እንዲሁም አዳማ ከተማ ከሸገር ሲቲ ጋር ያለ ግብ 0ለ0 ተለያይተዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ 0–0 ነገሌ አርሲ
በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ነገሌ አርሲ መካከል የተደረገው ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ የግብ ሙከራዎች በብዛት ባይታዩም ሮቦት ሰላሎ ከአቤል ሀብታሙ የተላከለትን ኳስ ታክል በማድረግ ያስቀረው ሙከራ ተጠቃሽ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ግብ ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የግብ እድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በተለይም በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች የግብ ፍለጋቸውን ቢያጠናክሩም የተፈለገውን ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። በመጨረሻም ጨዋታው 0ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ሀላባ ከተማ 1–0 ባህር ዳር ከተማ
ሀላባ ከተማ በባህር ዳር ከተማ ላይ ያስመዘገበው ድል የጨዋታው ተጠቃሽ ውጤት ሆኗል። በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ፉክክር ያደረጉ ሲሆን፣ ሀላባ ከተማ የግብ እድሎችን በመፍጠር ጥሩ አቋም አሳይቷል ። ሆኖም አጋማሹ ያለ ግብ ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ በ47ኛው ደቂቃ ሽመልስ ጉግሳ ከግራ መስመር ወደ ቅጣት ምት ሳጥን የላካትን ኳስ ዮናታን ኃይሉ ወደ ግብነት በመቀየር ሀላባ ከተማን ቀዳሚ አድርጓል።
ግቧን ካስቆጠሩ በኋላ ባህር ዳር ከተማ ጫናዋን በማሳደግ ወደ ግብ ለመድረስ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርገዋል ። ሆኖም የሀላባ ከተማን መረብ መድፈር አልቻለችም። በጨዋታው መገባደጃ የነበረው የደጋፊዎች ድባብም ለጨዋታው ድምቀት ጨምሯል።
በመጨረሻም ሀላባ ከተማ በዮናታን ኃይሉ ብቸኛ ግብ ባህር ዳር ከተማን 1ለ0 በማሸነፍ የሊጉን የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል ።

አዳማ ከተማ 0–0 ሸገር ሲቲ
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ምሽት 12:00 ሰዓት የተደረገው የአዳማ ከተማ እና ሸገር ሲቲ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ አቋም ያሳዩ ቢሆንም ወደ ግብ የቀረቡ ግልጽ ሙከራዎች በብዛት አልታዩም። አጋማሹም 0ለ0 ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ አዳማ ከተማ በፈጣን የጨዋታ ሽግግር ወደ ተጋጣሚዋ የግብ ክልል በመድረስ እድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። ሸገር ሲቲም በፈጣን መልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል ።
ሆኖም ሁለቱም ቡድኖች የግብ እድሎቻቸውን ወደ ግብነት መቀየር ባለመቻላቸው ጨዋታው ያለ ግብ 0ለ0 ተጠናቋል።


