ፕሪምየር ሊግ ትኩረት | ዳግማዊ አቡበከር ናስር?

ፕሪምየር ሊግ ትኩረት | ዳግማዊ አቡበከር ናስር?

የግብ አስቆጣሪዎች እጥረት በስፋት በሚስተዋልበት እግር ኳሳችን ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ሌላ አዲስ ተስፈኛ አጥቂን ይዘው ብቅ ብለዋል ፤ አቡበከር ናስርን ጀግናው ያደረገው ሌላኛው አቡበከር ናስር?

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁለት የሊግ ጨዋታዎች በ100% ክብረ ወሰን ሊጉን ሲጀምር ከቡድኑ ወሳኝ ድሎች ጀርባ አንድ ስም አለ ፤ ሄኖክ ኤርሚያስ።ለሊጉ ገና አዲስ የሆነው አጥቂው ሜዳ ላይ እያሳየ የሚገኘው ብቃት ግን ገና ሁለተኛ ጨዋታውን በሊጉ እያደረገ ሳይሆን ለሊጉ ቤተኛ የሆነ አጥቂን ይመስላል።

ፍጥነት ፣ የላቀ ፍላጎት ፣ የአስደናቂ የአጥቂ ደመ ነፍስ ፣ ግሩም የሆነ የቦታ አያያዝና አጨራረስ የተጫዋቹ መገለጫ ናቸው።በክረምቱ መዲናችን ላይ በተደረገ ውድድር በየጨዋታው የግብ ናዳ በማዝነብ ሄኖክ ኤርሚያስ የሚለውን ስም በስፓርት ቤተሰቡ ዘንድ ያስተዋውቅ እንጅ በተለይ የሀገሪቱን የዕድሜ እርከን ሊጎችን ለሚከታተሉ ግን ሄኖክ ኤርሚያስ የሚለው ስም ከፍ ያለ ተስፋ የተጣለበት አጥቂ መጠርያ ነበር።

ከዓመታት በፊት በአሰልጣኝ ቶፊቅ ከማል በሚመራውና በወቅቱ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን በሚያሰናዳቸው የዕድሜ እርከን ውድድሮች ተካፋይ በነበረው ዲኤፍቲ ቡድን ውስጥ 21 ግቦችን በማስቆጠር የውድድር ዘመኑን ያጠናቀቀውና በብዙዎች ዘንድ ዓይን ውስጥ የገባው ተጫዋቹ አስከትሎም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ታዳጊ ቡድኖች ውስጥ ባሳየው ድንቅ ብቃት ከዚህ ቀደም በአሰልጣኝ ዕድሉ ደረጀና ስዮም ከበደ መሪነት በሁለት አጋጣሚዎች ሀገሩን በመወከል በሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድሮች ላይ ተካፍሏል።

ታድያ እንዳለመታደል ሆኖ የአቡበከር ናስር አድናቂ እንደሆነ የሚናገረውና በአጨዋወት ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ከአቡበከር ናስር ጋር የሚመሳስለው አጥቂው በተደጋጋሚ ጉዳቶች መነሻነት በተፈለገው ልክ የእግር ኳስ ህይወቱ ወደፊት መስፈንጠር አልቻለም ፤ ዘንድሮ ግን ለወጣቶች ዕድልን በመስጠት በሚታወቀው አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ በሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው ቡድን ያገኘውን ዕድል በሚገባ በመጠቀም ላይ ይገኛል።

ከትላንቱ ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ስለ ወጣቱ አጥቂ የተጠየቁት አሰልጣኝ በፀሎት ሲመልሱ ብላቴናው ከጎል ጋር ያለውን ደመነፍስ አድንቀው ከኳስ ውጪ ያለውን ታታሪነትም እንዲሁ አሞካሽተዋል ፤ በተመሳሳይ የቡድን አጋሩ የሆነው ሙሉቀን አዲሱ ስለ ሄኖክ ሲናገርም የመጪው ዘመን የእግር ኳሳችን ተስፋ እንደሆነ ገልፆ ተጫዋቹ ገና አቅሙን እንዳላሳየም ምስክርነቱን ሰጥቷል።

አምና በሊጉ ባይተዋር ስም የነበረውን ናትናኤል ዳንኤልን ለሊጉ ጣምራ ከፍተኛ አስቆጣሪነት ያበቁት አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ዘንድሮ በተስፈኛው ሄኖክ ኤርሚያስ የጎል ፍላጎታቸውን በዘላቂነት ያስታግሱ ይሆን የሚለው ጉዳይ የሚጠበቅ ሆኖ ተስፈኛውን አጥቂ ወደ ዘላቂ ግብ አስቆጣሪነት ለማሸጋገር ክፍተቶቹን በስልጠና ከመሙላት ባሻገር ተጫዋቹ ካለው ተደጋጋሚ የጉዳት ታሪክ መነሻነት በክለቡ የአሰልጣኝ ቡድን ሆነ የህክምና ዲፓርትመንት ሰዎች ዘንድ ግን በጥንቃቄ ሊታገዝ ይገባል።

ምንም እንኳን እግር ኳስ የንክኪ ስፓርት እንደመሆኑ የተጫዋቹን እያንዳንዱን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ መገመት ሆነ መከታተል ባይቻልም ከጨዋታ ደቂቃ ፣ ከልምምድ ጫና እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አንፃር ይበልጥ በሜዳ ላይ የሚሰጠውን ግልጋሎት ለማሳደግ በልዩነት ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል።

በሁለት ጨዋታ አጀብ ያሰኘን ሄኖክ በቀጣይ እንደሚያደንቀው አቡበከር ናስር በሊጉ በወጥነት ያስደምመን ይሆን የሚለውን ጥያቄ ግን ጊዜ ምላሽ ይሰጠናል።