ፕሪምየር ሊግ ትኩረት | “ገብርዬ ጓርዲዮላ” ተብሎ የተዘመረበት የደርቢው ጨዋታ

ፕሪምየር ሊግ ትኩረት | “ገብርዬ ጓርዲዮላ” ተብሎ የተዘመረበት የደርቢው ጨዋታ

ቡናማዎቹ ጥሩ መሪ እንዲሁም ጫናን መቋቋሚያ “ጫንቃ” እንዳላቸው ያሳዩበት የደርቢው ጨዋታ ሌላው የሳምንቱ የትኩረታችን ማዕከል ነው።

​በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ትልቅ ቦታ ያላቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና እርስ በርስ የሚያደርጓቸው ፍልሚያዎች ሁልጊዜም ከውጤት በላይ ትልቅ ስሜት፣ ታክቲካዊ ሽኩቻ እና የደጋፊዎች ትዕይንት የሚታይባቸው ናቸው። ቅዳሜ ከሰዓት በሁለቱ ክለቦች መካከል የተደረገውና በኢትዮጵያ ቡና 2ለ1 አሸናፊነት የተጠናቀቀው ጨዋታም ከእነዚሁ የማይረሱ ፍልሚያዎች አንዱ ሆኖ አልፏል። ጨዋታው የደጋፊዎችን ስሜት ኮርኩሮ ከመጠናቀቁ በላይ የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን አሰልጣኝነት እና ታክቲካዊ ብስለት በግልጽ ያሳየ አጋጣሚ ስለነበረ የትኩረታችን ማዕከል አርገነዋል።

ታክቲካዊ በሆነ መነፅር በጨዋታው ​የአሰልጣኝ ገብረመድህን ትልቁና ደፋሩ ውሳኔ ቡድናቸውን በሦስት የተከላካዮች አደራደር ቅርፅ ቃኝተው ወደ ሜዳ ማስገባታቸው ነው። ቡድኑ ባልነው የሦስት የመሐል ተከላካዮች ጥምረት (በረከት፣ ድልአዲስ እና ራምኬል) እንዲሁም ሁለት የመስመሩን ኮሊደር በሚዘውሩ ተጫዋቾች (በፍቃዱ እና አብዱሰላም) ሳይገመት መቅረቡ በተወሰነ መልኩ ፈረሰኞቹን ሰርፕራይዝ ያደረገ ይመስላል። እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባሉ ፈጣን እና የማጥቃት አቅማቸው ከፍተኛ በሆኑ ክለቦች ላይ በሦስት ተከላካይ መጫወት ከፍተኛ ስጋት ያለው ቢሆንም አሠልጣኝ ገብረመድህን ግን የመሃል ሜዳውን የበላይነት ለመውሰድ፣ በመጀመሪያው የጊዮርጊስ ጨዋታ ፈረሰኞቹ በተደጋጋሚ ሲከተሉት የነበረውን የተሻጋሪ የማጥቂያ ኳሶች ለመመከት እና የጨዋታውን ፍጥነት ለመቆጣጠር ደፍረው የተገበሩት ታክቲክ ነበር። ይህ አቀራረብ ቡድኑ ኳስ በእግሩ ስር በሚሆንበት ጊዜ የመሃል ሜዳውን በቁጥር ብልጫ እንዲወስድ፣ ተቃራኒ ቡድን ላይ ጫና እንዲፈጥር እና በክንፎች በኩል ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሽግግሮችን (Transitional Play) በአግባቡ እንዲጠቀም ትልቅ ዕድል ሰጥቶታል። በመከላከሉም ረገድ ሦስቱ ቀመታም የመሐል ተከላካዮች የጊዮርጊስን ተሻጋሪ ኳሶች በቀላሉ እንዲቆጣጠሩ ያስቻለ ነበር።

​ከስልት ጥንካሬው ባሻገር የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች በጨዋታው ማጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ያሳዩት የአእምሮ እና የአካል ብርታት መደነቅ ያለበት ሌላኛው ነገር ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ውጤቱን ለማስተካከል እና ለመገልበጥ የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች ሙሉ በሙሉ በከፍተኛ ጫና በመጫወት ማጥቃትን መርጦ ነበር። ምርጫውንም በአራት አጥቂዎች እየመራ በጨዋታው አቻ ወይም ድል ለማግኘት ሲሞክር ነበር። ሆኖም የቡናማዎቹ ስብስብ በዲሲፕሊን የተዋቀረ መከላከል፣ ከፍተኛ ትኩረት እና ያልተደናገጠ የቡድን መንፈስ በማሳየት በተለይ በመስመሮች በኩል በአየር ላይ ሲፈጠሩ የነበሩትን ጫናዎች መቋቋም ችሏል። ይህ አደረጃጀት ቡድኑ በታክቲክ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአእምሮ ዝግጅትም በኩል በከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጫ ነው።

​በጨዋታው ማጠናቀቂያ ላይ ከስታዲየሙ መንፈስ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ሁነት ደግሞ ለዚህ ድል ልዩ ውበት ሰጥቶታል። የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች “ገብርዬ ጓርዲዮላ” እያሉ ያሰሙት ዝማሬ ለአሰልጣኙ የታክቲክ ብልህነት የተሰጠ ድንቅ እውቅና እና የደጋፊው ጥልቅ ፍቅር ማሳያ ነው። ይህ ዓይነቱ ድጋፍ የአሰልጣኙን እና የተጫዋቾቹን መተማመን የሚጨምር ከመሆኑም በላይ በሊጉ ውድድር ውስጥ የቡድኑን የዋንጫ ተወዳዳሪነት መንፈስ በእጅጉ የሚያጠናክር ነው።

​በአጠቃላይ የቅዳሜው የደርቢ ጨዋታ ለኢትዮጵያ ቡና ባለሦስት ነጥብ ድል ብቻ ሳይሆን አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በታክቲክ በኩል ያላቸውን ጥልቅ እውቀት እና የደፋር ውሳኔ ሰጪነት ብቃት ዳግም ያስመሰከሩበት እንዲሁም የተጫዋቾቻቸው ጫናን ውጦ የመጫወት አቅም ያሳየ ነበር ። ይህ ድል ቡድኑ ለቀጣይ ጨዋታዎች የሚያስፈልገውን ከፍተኛ የመንፈስ ጥንካሬ እና የመተማመን ስሜት ያጎናፀፈው ትልቅ ክስተት እንደሆነም ይታመናል።