ዋልያዎቹ 2ኛ የማጣርያ ሽንፈት አስተናገዱ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው የምድብ ማጣርያ ወደ ባላንታየር ተጉዞ በማላዊ ብሄራዊ ቡድን 3-2 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡

ጨዋታው በተጀመረ በ16ኛው ደቂቃ አቱሳዬ ንዮንዶ ግብ አስቆጥሮ ማላዊን መሪ ሲያደርግ የጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ ሊገባደድ 2 ደቂቃዎች ሲቀሩ በታደለ መንገሻ ተቀይሮ የገባው ጌታነህ ከበደ በ2 ደቂቃዎች ልዩነት ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ ግብ በማስቆጠር ኢትዮጵያን አቻ አድርጓል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ፍራንክ ባንዳ እንደ ጌታነህ ሁሉ ግብ አስቆጥሮ ማላዊን መሪ ለማድረግ በሜዳ ላይ መቆየት ያስፈለገው 2 ደቂቃዎች ነበሩ፡፡ከፍራንክ ግብ መቆጠር 2 ደቂቃዎች በኋላም አቱሳዬ ንዮንዶ የጨዋታው ሁለተኛ ግቡን አስቆጥሮ የማላዊን መሪነት ወደ 3-1 አስፍቶታል፡፡

የኢትዮጵያን ቀሪ አንድ ግብ በተጨማሪ ደቂቃ ያስቆጠረው በኡመድ ኡኩሪ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ዩሱፍ ሳላህ በቅጣት ምት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በምድቧ ያደረገቻቸውን ሁለት ጨዋታዋን ተሸንፋ የምድቡ የመጨረሻ ደጃን የያዘች ሲሆን ቀጣይ ጨዋታዋን ከ1 ወር በኋላ አዲስ አበባ ላይ ከማሊ ብሄራዊ ቡድን ጋር ታደርጋለች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *