የሴቶች ገፅ | የመጀመሪያው የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ አዝናኝ ክስተት…

ከዚህ ቀደም ከእግርኳስ ተጫዋችነት እስከ ህክምና ባለሙያነት የዘለቀውን የዶ/ር እንደገናዓለም አዋሶን አስገራሚ ህይወት አቅርበንላችሁ ነበር። ዛሬ ደግሞ የመጀመሪያው የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሲመሰረት ተጫዋቾቹ የሰሩትን አስቂኝ ድርጊት እንደገናዓለም ታጫውተናለች።

ከአዳማ ከተማ 09 ቀበሌ ተነስታ ሃገሯን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ መወከል የቻለችው እንደገናዓለም በተለይ በግራ እግሯ በምትሰራቸው ተዓምሮች የብዙዎችን ቀልብ ገዝታ ቆይታለች። ከምንም በላይ ደግሞ ከርቀት በግራ እግሮቿ የምታስቆጥራቸው ጎሎች ከስሟ በላይ “ባለግራ እግሯ” የሚል ተቀፅላ እንዲሰጣት አስችሏል። በዞን፣ ወረዳ እና ክልል ደረጃ ስትጫወት ባሳየችው ምርጥ ብቃት አማካኝነት ወደ መጀመሪያው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የተካተተችው ተጫዋቿ ለዛሬ በጊዜው (1994) የነበረውን ነገር ወደ ኋላ መለስ ብላ በአጭሩ ታስታውሰናለች።

“የመጀመሪያው የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ለእኔ ልዩ ትዝታ አለው። ጥሩ ጊዜ ነበረን። ከዛ በፊት ግን ለዞን እና ቀበሌ ለመጫወት አሰልጣኜ እቤት እየመጣ አባቴን በስንት መከራ እየለመነ ነበር የሚያስፈቅድልኝ። በውድድር ላይ ደግሞ ጎል አግብቼ ስመለስ የሰፈሩ ሰው ግልብጥ ብሎ ነው ቤታችን የሚመጣው። አባቴን እንኳን ደስ አለህ ለማለት። ብቻ ከዚህ ውድድር ተነስቼ ለብሄራዊ ቡድን ተመረጥኩ። የመጀመሪያው የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ስብስብ የሚመራ የነበረው በአሰልጣኝ አዳነ፣ በለጥሽ እና አሸናፊ አማካኝነት ነበር። አሁን ላይ ወደኋላ መለስ ብዬ የነበረንን ፍቅር እና አንድነት ሳስታውስ በጣም ነው የሚገርመኝ። ከምነግርክ በላይ ደስ የሚል ጊዜ ነበር። አብዛኞቻችን ተጫዋቾች ደግሞ ከክልል ነበር ተመርጠን የመጣነው። በተጨማሪም ገና ታዳጊዎችም ስለነበርን አልበሰልንም ነበር። ምንም ይሁን ምንም ግን እርስ በእርሳችን በጣም ነበር የምንዋደደው። እንደውም ከጨዋታ ሁለት እና ሶስት ቀን በፊት ምርጫ ሲኖርና ተጫዋቾች ከመካከላችን ሲቀነሱ እናለቅስ ነበር። ለምን ይቀነሳሉ ብለን እራሱ ምግብ አንበላም ያልንበት እና ያኮረፍንበት ጊዜ ነበር። በዚህ ደግሞ አሰልጣኞቹ የተቀነሰችውን ተጫዋች ለመንገር ተቸግረው እና ተጨንቀው ያቃሉ። ብቻ የነበረንን ስሜት ለመንገር ቃላት ያጥረኛል።”

ጥሩ ጊዜን እንዳሳለፉ እያወጋችን ያለችው እንደገና የመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታቸውን ወንጂ ላይ ሲያደርጉ የሰሩትን አስቂኝ ተግባር ደግሞ ትነግረናለች።

“ጨዋታው ከዩጋንዳ ጋር ነበር። ቀድሜ እንዳልኩክ የመጀመሪያዎቹ የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ስለሆንን ደስ የሚል ስሜት ተሰምቶናል። በደስታው ልክ ግን ፍርሃትም ነበር። ስታዲየሙም ደግሞ በደጋፊዎች መሞላቱ አስደንግጦን ነበር። የሆነው ሆኖ ግን እየተደናበርንም ቢሆን ወደ ሜዳ ገባን። የብሄራዊ ቡድን ጨዋታ እንደመሆኑ የህዝብ መዝሙር መዘመር ነበረበት። ከጨዋታው በፊት የኢትዮጵያን ብሄራዊ የህዝብ መዝሙርን እየደጋገምን አጥንተን ነበር። ነገርግን ሜዳ ላይ ቆመን መዝሙሩን ከደጋፊዎች ጋር ስንዘምር ተኮለታተፍን። ፍርሃቱ እና ጭንቀቱ ነው መሰለኝ እንደ ስማችን የያዝነው የሃገራችን ብሄራዊ መዝሙር ከነአካቴው ጠፋብን። እንደውም ቋሚ ከነበርነው ውስጥ 7 ወይንም 8 ተጫዋቾች ገና መዝሙሩ ሳያልቅና ህዝቡ እየዘመረ ያለቀ መስሎን ማጨብጨብ እና መዝለል ጀመርን። ይህም ደሞ የሆነው ስለደነገጥን እና ስሜታችን ስለተረባበሸ ነው።”

በፍርሃት ስሜት ጨዋታውን የጀመሩት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ቀስ በቀስ በውስጣቸው የነበረው መደናገጥ እና ፍርሃት እየተነነ መጥቶ ሁለት ጎሎች አስቆጥረው ጨዋታውን አሸንፈው ወጥተዋል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ