የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ማጣርያ ጨዋታ በዓመቱ መጨረሻ ይቀጥላል

በኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት ከቅድመ ማጣርያ መሻገር ያልቻለው የ2020 የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ማጣርያ በነሐሴ ወር እንደሚጀምር ካፍ ለፌዴሬሽኖች አሳውቋል።

በቅድመ ማጣርያው ብሩንዲን በድምር ውጤት 7-1 አሸንፎ ወደ አንደኛ ዙር ያለፈው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በቀጣይ ዙር ግንቦት ላይ ከዚምባብዌ ጋር ለመጫወት መርሐ ግብር ቢወጣለትም በወረርሺኙ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ የሚታወስ ሲሆን ካፍ ባወጣው አዲስ መርሐ ግብር የመጀመርያው ጨዋታ ከነሐሴ 28-30 ፤ የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ከጳጉሜ 5-መስከረም 2 ይደረጋል። ኢትዮጵያ ዙሩን ካለፈች በሁለተኛው ዙር ጥቅምት ወር ላይ ከቦትስዋና እና ደ/አፍሪካ አሸናፊ የምትጫወት ይሆናል።

ፌዴሬሽኑ በስሩ የሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖችን ውል አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ እና ቀጣይ ውድድሮች ካለመታወቃቸው ጋር በተያያዘ እንደማያራዝም ማሳወቁ የሚታወስ ሲሆን የ20 ዓመት በታች ሴቶች ማጣርያ የሚደረግበት ጊዜ በመታወቁ የቡድኑ አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል እና ረዳቶቹ ምናልባትም ውላቸው ሊታደስላቸው እንደሚችል ይገመታል።

በ2020 ሊደረግ ታስቦ የነበረው የዓለም ዋንጫው ጥር 2021 ላይ በኮስታሪካ እና ፓናማ አዘጋጅነት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ