ሰበታ ከተማ የነበረበትን ችግር ከነገ ጀምሮ እንደሚፈታ አስታወቀ

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና በተጫዋቾቹ ሲወቀስ የከረመው ሰበታ ከተማ የነበረበትን ችግር ከነገ ጀምሮ ለመፍታት ማቀዱን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡

ከስምንት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የተቀላቀሉት ሰበታ ከተማዎች ወደ ሊጉ ዳግም ብቅ ሲሉ በርካታ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾችን ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር ማምጣታቸው ይታወሳል። ይሁን እና ክለቡ ከሊጉ መቋረጥ ጊዜ አንስቶ በአሰልጣኙ እና ተጫዋቾቹ አማካኝነት ከፍተኛ ቅሬታን ሲነሳበት ቆይቷል፡፡ በተለይ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ “ለእኔም ሆነ ለተጫዋቾቹም መፈፀም የነበረበት ክፍያ አልተፈፀመም። ሌሎች ተጓዳኝ ጥቅማጥቅሞችም በስምምነታችን መሠረት አልተፈፀም። ይህ ካልሆነ ግን ከክለቡ ጋር ለመለያየት እገደዳለሁ” ሲሉ የቅሬታ ደብዳቤን ከቀናት በፊት ለክለቡ ማስገባታቸው ይታወሳል።

ከአሰልጣኙ ጎን ለጎን የክለቡ ተጫዋቾች “ለእኛም ደመወዝ አልተፈፀመልንም። ይከፈለን! ካልሆነ ደግሞ ውላችን ይቋረጥልን” በማለት ጥያቄያቸውን በክለቡ ላይ በተደጋጋሚ ሲያነሱ ሰንበትበት ብለዋል፡፡

ይህንን ጉዳይ ለመፍታትም ባለፈው ሳምንት ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር የከተማውን ከንቲባ ጨምሮ የክለቡ ቦርድ አባላት ባሉበት ውይይት ያደረጉት ሰበታዎች የተነሱትን ጥያቄ ለመመለስ ከስምምነት መድረሳቸው ተነግሯል። አሰልጣኝ ውበቱ አባተም በክለቡ ለመቀጠል ተስማምተው ለ2013 የውድድር ዘመን ተጫዋች ወደ ማስፈረሙ ስራ መግባት መጀመራቸውን ሰምተናል፡፡

የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ምንዳ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከነገ ጀምሮ ለተጫዋቾቹ የደመወዝ ክፍያን ለመፈፀም ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የገለፁ ሲሆን ውላችን ይቋረጥ ያሉ ተጫዋቾች ለሚዲያ ከመናገራቸው ውጪ ወደ ክለቡ መተው ጥያቄን እንዳላቀረቡ ተናግረዋል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ