ከፍተኛ ሊግ | ወልዲያ ስምንት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈረመ

በቅርቡ አዲስ አሰልጣኝ የቀጠረው ወልዲያ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል፡፡

ከሊጉ ከወረደ በኃላ ያለፉትን ሦስት የውድድር ዓመታት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ እየተወዳደረ የሚገኘው ክለቡ የሊጉ ልምድ አላቸው የሚባሉት አሰልጣኝ መኮንን ገብረዮሐንስን ከቀናት በፊት መሾሙ ይታወሳል፡፡ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አድነው ምህረቴ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት “ካለፉት አመታት በተሻለ መጫወት የሚችል ቡድን እንዲሆን እና ወደ ፕሪምየር ሊጉ በ2014 መግባት እንዲችል ጠንካራ አሰልጣኝ ቀጥረናል። ለዚህም ስንል ጥሩ አሰልጣኝ እና ጠንካራ ተጫዋቾችን ማስፈረም ጀምረናል።” ብለዋል፡፡

ክለቡም ለውድድሩ ጠንክሮ ለመቅረብ ስምንት ተጫዋቾችን ከተለያዩ ክለቦች አስፈርሟል፡፡ ከሀዋሳ ከተማ ታዳጊ ቡድን የተገኘውና አምና በኢኮስኮ ሲጫወት የነበረው ወጣቱ ግብ ጠባቂ መስፍን ሙዜ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከአሰልጣኙ ጋር የሰራው ሌላው ጎል ጠባቂ ምናለ በቀለን፣ ተከላካዮቹ እስካድማስ ከበደ (ከደሴ ከተማ)፣ አሳልፈው መኮንን (ከኢትዮ ኤሌክትሪክ)፣ ዳግማዊ ዓባይ (ከኢኮስኮ)፣ የቀድሞ የቡድኑ አማካይ ምንያህል ይመር (ከአዲስ አበባ ከተማ) ፣ ጅላሎ ሻፊ (ከቡራዩ ከተማ) እንዲሁም ከዚህ ቀደም በወልዲያ የተጫወተው አጥቂው ፍፁም ደስይበለው አዳዲሶቹ የወልዲያ ፈራሚዎች ናቸው፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!