“የእግርኳስ እድገቴ በጣም ፈጣን ነው፤ እየተሻሻለም መጥቷል” – አቡበከር ናስር

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታውን ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም አድርጎ ለረጅም ደቂቃዎች በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር ፋሲል ከነማን የረታው ኢትዮጵያ ቡና ቁልፍ ተጫዋች ከሆነው አቡበከር ናስር ጋር ቆይታ አድርገናል።

በቅርቡ ለኢትዮጵያ ቡና ለመቆየት የአምስት ዓመት ኮንትራት በመፈረም ለክለቡ ያለውን ታማኝነት በተግባር አሳይቷል። በሁሉም የዕድሜ እርከኖች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለው አጥቂው በየዓመቱ እድገቱ እየጨመረ መጥቶ በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ቡድን ውስጥ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን እያሳየ ይገኛል። በ2013 የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጥሩ አጀማምር ከማድረጉ በተጨማሪ ከወዲሁ በሁለት ጨዋታ ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር ከፍተኛ ጎል አግቢነትን እየመራ ይገኛል። በዚህ ወጥ አቋሙ መዝለቅ ከቻለ የኮከብነት ተፎካካሪነት ውስጥ መግባቱ እንደማይቀር ይገመታል። አቡበከር ናስር ስለ ውድድር አጀማመሩ እና ስለ ቀጣይ ዕቅዱ ከዛሬው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

” የዘንድሮ አጀማመሬ እስካሁን በሁለት ጨዋታ አሪፍ ነው። ባሳለፍነው ሳምንት ከወልቂጤ ጋር ውጤት ማስጠበቅ አቅቶን አቻ ወጥተን ነበር። ዛሬ ደግሞ የነበረብንን ድክመት አሻሽለን በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ለማግኘት በነበረን ከፍተኛ ፍላጎት የምንፈልገውን አሳክተናል። እኔም በግሌ በሜዳ ውስጥ እስከቆየሁበት ጊዜ ድረስ ጎል አስቆጥሬያለው። በቀጣይ ከዚህ ተነስተን የተሻለ ነገር ይዘን እንቀርባለን።

” ከጨዋታው አስረኛው ደቂቃ ጀምሮ አሞኝ ነበር። ሆኖም መጫወት ስላለብኝ ነው የቆየሁት፤ መጨረሻም ተቀይሬ የወጣሁት በጉዳት ነው። ለቀጣይ ጨዋታ እደርሳለው ብዬ አስባለሁ።

” የእግርኳስ እድገቴ በጣም ፈጣን ነው፤ እየተሻሻለም መጥቷል። እዚህ ለመድረስ ብዙ ጥሬያለሁ። ከፈጣሪ ጋር የበለጠ ለመሥራት እጥራለሁ። ዘንድሮ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እናስባለን። ይሄም በአንድ ሁለት ጨዋታ እየታየ ነው። ያለየብንን ድክመቶች አስተካክለን በየጨዋታዎቹ የሚጠበቁብንን ለማድረግ እንሰራለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ