ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ ተከታታይ ድሉን አሳክቷል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ረፋድ ላይ ባህር ዳርን ከሀዋሳ ያገናኘው ጨዋታ በሀዋሳ የበላይነት ተጠናቋል።

ሁለቱም ቡድኖች በመጨረሻው የአዲስ አበባ ጨዋታዎቻቸው ድል ያስመዘገቡበት ስብስብ እና አደራደር ላይ ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በጨዋታው መጀመርያ አስር ደቂቃዎች ባህር ዳር ከተማዎች ከተከላካይ ጀርባ በሚጣል ኳስ በተደጋጋሚ ወደ ሀዋሳ የጎል ክልል በመድረስ ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም ወደ ጠንካራ ሙከራነት ለመለወጥ ግን ተቸግረው ታይተዋል።

መልካም በቀላሉ ኳሶችን ሲያመክኑ የታዩት ባህር ዳሮች በ21ኛው ደቂቃ መሪ የሚሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። ባዬ ገዛኸኝ ያመቻቸለትን ኳስ ግርማ ዲሳሳ ከሳጥኑ ጠርዝ መትቶ ሜንሳህ ሶሆሆ ቢያድነውም የተመለሰውን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ሳለአምላክ ተገኝ አስቆጥሮታል።

የተቀዛቀዘ አጀማመር ያደረጉት ሀዋሳዎች ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ ጨዋታውን የጀመሩ በሚመስል መልኩ ተነቃቅተው መንቀሳቀስ ችለዋል፤ ፈጣን ምላሽ ለመስጠም አልዘገዩም። በ24ኛው ደቂቃ ደስታ ዮሐንስ ከግራ መስመር ያሻገረውን ግሩም ኳስ መስፍን ታፈሰ በግራ እግሩ በጥሩ አጨራረስ መትቶ ሀዋሳን አቻ አድርጓል።

ሁለቱ ጎሎች ከተቆጠሩ በኋላ ጨዋታው ጥሩ ፉክክር ቢያስተናግድም የጠራ የጎል ሙከራ በቀሪዎቹ የመጀመርያው አጋማሽ ደቂቃዎች ሳያሳየን ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማዎች ኤፍሬም አሻሞን በወንድማገኝ ማዕረግ ቀይረው በማስገባት የተጫዋቾች አደራደር ላይ ለውጥ በማድረግ ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን የለውጡን ፍሬ ለመመልከት ብዙ አልቆዩም። በ59ኛው ደቂቃ ኤፍሬም አሻሞ ከወንድማገኝ ኃይሉ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን ውጪ ወደ ቀኝ ካደላ ቦታ በቀጥታ መትቶ ሀዋሳን ወደ መሪነት ያሸጋገረ ግሩም ጎል አስቆጥሯል። ለጎሉ መቆጠር የሀሪስተን ሄሱ የአቋቋም ስህተትም አስተዋፅኦ ነበረው።

ሀዋሳዎች ከመሪነት በኋላ ውጤት በማስጠበቅ ላይ ትኩረት ሲያደርጉ ባህርዳሮች የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ከርቀት በሚሞከሩ እና ከቆሙ ኳሶች የአቻነት ጎል ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። ባዬ ገዛኸን በሁለት አጋጣሚ ከርቀት የሞከራቸው ኳሶች እና በ84ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ሰለሞን ወዴሳ ሞክሮ ሜንሳህ በድንቅ ሁኔታ ያወጣበት ሙከራዎችም የሚጠቀሱ ነበሩ። ሆኖም ሀዋሳዎች መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ ጨዋታው በሀዋሳ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች መስፍን ታፈሰ በደረሰበት ግጭት ጭንቅላተሐ ተጎድቶ ህክምና ሲደረግለት ተመልክተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ