ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ድሉን አሳካ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሰባተኛ ሳምንት የበዐል ዕለት ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ ጌዲኦ ዲላን 1 ለ 0 አሸንፏል፡፡

10:00 ሲል በጀመረው እና ብዙ ማራኪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ባልተመለከትንበት ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በሚባክኑ እንቅስቃሴዎች የተሞላ ከመሆኑ ባሻገር ክለቦቹ ለማጥቃት ያላቸው ጥረት በስህተት የታጀበ ነበር፡፡ በተለይ ጌዲኦ ዲላ ከሚታወቅበት የመስመር አጨዋወት በዛሬው ጨዋታ ወጣ ባለ መልኩ በጥልቀት ለመንቀሳቀስ የሞከሩ ቢሆንም ወጥነት ይጎለው ስለነበር ግብ ጋር ከደረሱ በኃላ ፍፃሜያቸው እጅጉን ደካማ ነበር፡፡

ሆኖም በፍላጎት በመጫወት ታታሪነት በውስጣቸው ይታይባቸው የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ያለፉትን ሳምንታት ሽንፈቶቻቸውን በመርሳት አሸንፎ ለመውጣት ያላቸውን ኃይል አሟጠው ለመጠቀም ተግተዋል፡፡ በቀኝ በኩል የነበረችው እምወድሽ አሸብር ወደ ሳጥን ሰብራ በመግባት በተደጋጋሚ ለጌዲኦ ተከላካካዮች ፈተና ስትሆንም በሚገባ መመልከት ችለናል፡፡ ይሁንና የጠሩ ግልፅ አጋጣሚዎችን ያላየንበት ጨዋታ ያለ ጎል ወደ መበልሻ ቡድኖች እንዲያመሩ ሆኗል፡፡

ከእረፍት መልስ በተሻለ ተነሳሽነት ተጫውቶ ለመውጣት ወደ ሜዳ የገቡት ጌዲኦ ዲላ በርካታ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ የግብ ክልል የደረሱበት ነገር ግን የአጥቂዋ ቱሪስት ለማ እና ባለ አስገራሚ ክህሎቷ እፀገነት ግርማ እጅጉን ተቀዛቅዘው መታየታቸው በፍላጎት እና በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት በሚጥሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ለመበለጥ ተገደዋል፡፡ በዚህም 60ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ተቆጥሮበታል፡፡ የአዲስ አበባ አጥቂ ቤተልሄም ሰማን ወደ ግብ ኳስን ስትመታ ተከላካይዋ ደመቀች ዳልጋ ኳስን በእጅ በመንካቷ የተሰጠውን የፍፃም ቅጣት ምት ቤተልሄም ታምሩ ወደ ጎልነት ለውጣው አዲስ አበባን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡

ጎል ካስተናገዱ በኃላ ሙሉ ኃይላቸውን በማጥቃቱ ላይ አድርገው ብልጫን ወስደው መጫወት የቻሉት ዲላዎች በእፀገነት ግርማ ያለቀላቸው ሁለት ኳሶች ቢያገኙም ግብ ጠባቂዋ ቤተልሄም ዮሀንስ መልሳባታለች፡፡ አስጠብቆ ለመውጣት በየሜዳው የአዲስ አበባ ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ሲተኙ የታየ ሲሆን ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት 1 ለ 0 ተጠናቋል፡፡ ድሉም በተደጋጋሚ ሽንፈት ለገጠመው አዲስ አበባ የመጀመሪያ ድሉ ሆኖ ተመዝግቦለታል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት የአዲስ አበባዋ የመስመር ተጫዋች እምወድሽ አሸብርን የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ