ለፋሲል ከነማ ዲጂታል የመረጃ አስተዳደር ሊለማለት ነው

የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ፋሲል ከነማ ዘመናዊ የዲጂታል የመረጃ አስተዳደር ሊለማለት መሆኑን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በ54 ነጥቦች የ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ክለብ የሆነው ፋሲል ከነማ ተቋማዊ መዋቅሩን ለማሻሻል የተለያዩ ስራዎችን እንደጀመረ መግለፁ አይዘነጋም። ከሚሰሩት ስራዎች መካከል ደግሞ አንደኛው ክለቡን ወደ ዘመናዊ መንገድ የሚያስገቡ ሁነቶች እንደሆኑ ተነግሯል። ከእነዚህ ስራዎች መካከል አንዱ የሆነው የዲጂታል የመረጃ አስተዳደር ደግሞ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሊለማ መሆኑ ተሰምቷል።

ዲጂታል የመረጃ አስተዳደሩ የፋሲል ከነማ የስፖርት ቡድንን መረጃ ለደጋፊዎቹ እና ለማህበርሰቡ ባሉበት ለማድረስ የሚያስችል ነው ተብሏል። የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ ከፋሲል ከነማ ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የቦርድ አመራሮች ጋር ቡድኑን የዲጂታል ፖርታል ባለቤት ማድረግ በሚቻልበት ዙሪያ መክረዋል። ዲጂታል የመረጃ አስተዳደሩ ከፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ሊንክድኢን ከመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች እና ከቴሌ ብር ጋር በማገናኘት አገልግሎት መስጠት የሚያስችልም እንደሆ ታውቋል። የፋሲል ከነማ የስፖርት ቡድን ዲጂታል የመረጃ አስተዳደር በአንድ ወር ጊዜ አልመተን እናስረክባለን ሲሉ ዶክተር አህመዲን መሐመድ መግለፃቸውንም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በድህረ-ገፁ አስነብቧል።

ሚኒስቴር ድኤታው ጨምረውም እንደ ሀገር የተጀመረውን የዲጂታል ጉዞ ወደ ሁሉም ዘርፎች ለማውረድ እንሰራለንም ብለዋል። የፋሲል ከነማ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አብዮት ብርሃኑ በበኩላቸው ባለሙያዎችን በማሟላት የመረጃ አስተዳደሩ ሳይቆራረጥ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። ዲጂታል የመረጃ አስተዳደር ስርዓቱ የክለቡን ታሪክ፣ ዕለታዊ የእንቅስቃሴ መረጃ፣ የገቢ ማስገኛ ሽያጭ፣ የደጋፊዎች መረጃ፣ ድጋፍ ማሰባሰቢያ እና የመሳሰሉትን መረጃዎች አስተሳስሮ እንደሚይዝ ከሚኒስቴሩ መረጃ አግኝቻለሁ ብሎ ፋና አስነብቧል።