አዲስ አዳጊዎቹ ሦስት ዝውውሮችን አጠናቀዋል

በቀጣይ የውድድር ዓመት በፕሪምየር ሊጉ ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ የሚገኙት ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ሦስት ተጫዋቾች አስፈርመዋል።

በአሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ እየተመሩ በሀዋሳ ዝግጅታቸው የጀመሩት ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ከዚህ ቀደም ከከፍተኛ ሊግ አምስት ተጫዋቾችን ያፈረሙ ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ፊታቸውን በማዞር ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾች አስፈርመዋል።

ተከላካይ አማካዩ ብሩክ ቃልቦሬ ለክለቡ የፈረመ የመጀመርያው ተጫዋች ሆኗል። ከዚህ ቀደም በወልድያ ፣ ወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ በመጫወት ዓመቱን ያገባደደው ይህ አማካይ በቀጣይ ዓመት ለአዲስ አዳጊዎቹ ለመጫወት ፊርማውን አኑሯል።

ሁለተኛው ክለቡን የተቀላቀለው ተጫዋች ደግሞ አቤል ከበደ ነው። በመቻል ፣ ወልድያ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ተጫውቶ ያሳለፈው አቤል በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በድሬዳዋ ከተማ ቆይታ የነበረው ሲሆን መዳረሻው ሀምበሪቾ ዱራሜ ሆኗል።

ሦስተኛው ክለቡን የተቀላቀለው ተጫዋች ተከላካዩ ፀጋሰው ድማሙ ነው። ከዚህ ቀደም በሀድያ ሆሳዕና ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን የተጫወተው ይህ ተጫዋች በቀጣይ የውድድር ዓመት በአሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ ለሚሰለጥኑት ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ለመጫወት ፌርማውን አኑሯል።