ሴቶች 2ኛ ዲቪዚዮን | አቃቂ መሪነቱን ሲያስቀጥል ቂርቆስ ደረጃውን አሻሽሏል

በ6ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም እና በክልል ከተማ ቀጥለው ሲደረጉ አቃቂ ክፍለ ከተማ በድንቅ ግስጋሴያቸው በመቀጠል በመሪነታቸው ቀጥለዋል። ቂርቆስ ሲያሸንፍ ሻሸመኔ እና ፋሲል አቻ ተለያይተዋል፡፡

በ9 ሰዓት የሊጉ መሪ የሆነው አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማን የሊጉ ግርጌ ላይ ከሚገኘው ቦሌ ክ/ከተማ ያገናኘው ጨዋታ አቃቂዎች በመጀመሪያ አጋማሽ አከታትለው ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ታግዘው ቦሌን 2ለ1 ማሸነፍ ችለዋል፡፡ አቃቂዎች ፍፁም የበላይ በነበሩበት የመጀመሪያው አጋማሽ በ16ኛው ዙፋን ደርፈሻ ወደ ግራ ያደላውን ቅጣት ምት በቀጥታ በመምታት ግሩም ግብን ማስቆጠር ችላለች፡፡ በተመሳሳይ በ18ኛው ደቂቃ ላይ የአቃቂዋ የመስመር አጥቂ ሠላማዊት ጎሳዬ በቦሌ ክፍለከተማ ግብጠባቂ ቃልኪዳን ገዛኸኝ ስህተት ታግዛ የቡድኗን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ያደረገችውን ሁለተኛ ግብ አስቆጥራለች። በጨዋታው ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለችው ዙፋን ዲርፈሻ በተመሳሳይ ወደግራ አድልቶ ያገኙትን የቅጣት ምት በተመሳሳይ በቀጥታ ወደ ግብ የላከችው ኳስ የግቡ አግዳሚ ሊመልስባት ችሏል፡፡

ቦሌዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መንቀሳቀስ በቻሉበት በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች አዝናኝ የሜዳ ላይ ፉክክርን ማሳየት ጨዋታው 2ለ1 በሆነ ውጤትሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ በጨዋታው መገባደጃ በተቃረበበት ወቅት ሜሮን አበበ ቦሌን ከባዶ መሸነፍ የታደገች ግብን አስቆጥራ ችላለች፤ በዚህም ውጤት መሠረት አቃቂዎች ነጥባቸውን ወደ 16 በማሳደግ በመሪነታቸው ቀጥለዋል፡፡

በመጠቀጠል በ11:00 ተመጣጣኝ ፉክክርን ባስተናገደው የቂርቆስና ልደታ ክ/ከተማ ጨዋታ በቂርቆስ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጀምሮ በሙከራዎች ታጅቦ በተካሂደው በዚሁ ጨዋታ ገና በ5ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በግሩም ሁኔታ የተሻረላትን ኳስ በቄንጠኛ አጨራረስ የቂርቆሷ ትሁን ፋሎ አስቆጥራ ቡድኗን ቀዳሚ ማረግ ችላ ነበር፡፡ተመጣጣኝ እና ሁለቱም ቡድኖች ማጥቃት ላይ መሠረት ያደረገ አጨዋወትን እንደመምረጣቸው ለተመልካች አዝናኝ የነበረ የጨዋታ አጋማሽ ነበር ፤ በዚሁ አጋማሽም በሁለቱም ቡድኖች በኩል በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች ተስተናግደዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ቂርቆሶች የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፤ በዚህም በርካታ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ግብ ግን ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ የቂርቆሷ ግብጠባቂ ዓይናለም ሻታ እጅግ ድንቅ የሚባል ብቃቷን ባሳየችበት በዚሁ አጋማሽ በርካታ ያለቀላቸው ኳሶችን አምክናለች፡፡ ጨዋታው በቂርቆስ የ1ለ0 አሸናፊነት መጠነቀቁን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ 10 ከፍ በማድረግ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችለዋል፡፡

በ9:00 ሻሸመኔ ላይ በ10 እና 8 ነጥቦች 3ኛ እና 4ኛ የነበሩት ሻሸመኔ ከተማ እና ከፋሲል ከነማኔ ያገናኘው ጨዋታ 0ለ0 በሆነ የአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

ትላንት በተደረገ ብቸኛ መርሐ ግብር አዲስ አበባ ስታድየም ላይ መቐለ 70 እንደርታ ባለሜዳው ንፋስ ስልክን 5-1 አሸንፏል። ዮርዳኖስ በርኸ ሁለት ጎሎችን ስታስቆጥር ሠላም ተክላይ፣ ርሻን ብርሀኑ እና አበባ ገብረመድህን የቀሪኮቹ ግቦች ባለቤት ናቸው። ማህሌት በቀለ ደግሞ የንፋስ ስልክን ብቸኛ ጎል አስቆጥራለች።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *