ሴቾች 1ኛ ዲቪዝዮን | ንግድ ባንክ በመሪነት ሲቀጥል መከላከያ፣ አዳማ እና ሀዋሳም አሸንፈዋል

በስምንተኛው ሳምንት የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ሦስት ጨዋታዎች ተካሂደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አዳማ ከተማ መከላከያ እና ሀዋሳ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

ሀዋሳ ላይ በ8:00 ድሬዳዋ ከተማን ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ በምርቃት ፈለቀ ግቦች 2-0 አሸንፏል። በአጫጭር ቅብብሎች ተጋጣሚያቸውን ተጭነው መጫወት የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች በአብዛኛው የመጀመሪያው አጋማሽ ደቂቃዎች የበላይነት ነበራቸው። ወደ ግራ መስመር ተመላላሿ ካሰች ፊሳ ባደላ ማጥቃትም በተደጋጋሚ በድሬዎች ሳጥን ዙሪያ ሲገኙ ይታይ ነበር። በተለይም የቡድኑ ጥቃት ዋነኛ ትኩረት የነበረችው  ምርቃት ፈለቀ 10ኛው ደቂቃ ላይ በግል ጥረቷ ከሳጥን ውስጥ ያደረገችው ሙከራ እና ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ለነፃነት መና አቀብላት ነፅነት አክርራ የመታችው ኳስ በድሬዳዋ ግብ ጠባቂ አክሱማዊት ጥረት የዳኑ ነበሩ። ሆኖም አክሱማዊት ምርቃት ላይ በሰራችው ጥፋት ሀዋሳዎች 26ኛው ደቂቃ ላይ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ምርቃት ራሷ መትታ ማስቆጠር ችላለች። 


ይመችሽ ዘውዴ እና ስራ ይርዳው አማካይነት አልፎ አልፎ ወደግብ ይደርሱ የነበሩት ድሬደዋዎች 37ኛው ደቂቃ ላይ ይመችሽ ከቅጣት ምት በተነሳ ኳስ ከቅርብ ርቀት ካደረገችው ሙከራ ውጪ እምብዛም የግብ ዕድል አልፈጠሩም። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ  በተሻለ ሁኔታ ለሀዋሳ የሜዳ አጋማሽ ቀርበው መጫወት ቢችሉም ጠንካራ ሙከራ ሳያደርጉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል። 


ከእረፍት መልስ ድሬዎች ተቀይራ በገባችው ነብያት ሀጎስ የፊት መስመር እንቅስቃሴ ተነቃቅተው ታይተዋል። ነገር ግን አሁንም የግብ ሙከራዎችን በማደረጉ በኩል ተዳክመው ታይተዋል። በአንፃሩ 72ኛው ደቂቃ ላይ ምርቃት የፊት መስመር አጣማሪዋ ነፃነት ከቀኝ መስመር ያደረሰቻትን ኳስ ተጠቅማ ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር የሀዋሳን መሪነት አስፍታለች። ከግቡ በኋላም ሀዋሳዎች በካሰች አማካይነት ሌላ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገዋል። ጨዋታው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች እየተቀዛቀዘ ሄዶ ረጃጅም ኳሶችን በተደጋጋሚ ወደ ፊት የጥሉ የነበሩት ድሬዎች ውጤቱን ማጥበብ ሳይችሉ ሀዋሳዎች 2-0 ማሸነፍ ችለዋል።


ወደ አሰላ ያቀናው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥሩነሽ ዲባባን 1-0 አሸንፏል። ባንክ በድሉ ተጠቅሞ ከተከታዩ በሁለት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል። 

04:00 ላይ በመከላከያ ሜዳ ጥረት ኮርፖሬትን የገጠመው መከላከያ 2-0 ማሸነፍ ችሏል። የምስራች ላቀው እና ሲሳይ ገብረዋህድ የመከላከያን ሁለት የድል ጎሎች ማስቆጠር የቻሉ ተጫዋቾች ናቸው። 

አዳማ ላይ አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው አዳማ ከተማ 3-1 በማሸነፍ ንግድ ባንክን መከተሉን ቀጥሏል። ሴናፍ ዋቁማ የዓመቱ 8ኛ ጎሏን ስታስቆጥር ሰናይት ቦጋለ እና ሰርካዲስ ጉታ ሌሎቹ ግብ አስቆጣሪዎች ናቸው።

8ኛ ሳምንት
ቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2011
ኢትዮ ኤሌክትሪክ 0-3 ቅዱስ ጊዮርጊስ
እሁድ ጥር 5 ቀን 2011
መከላከያ 2-0 ጥረት ኮርፖሬት
ሀዋሳ ከተማ 2-0 ድሬዳዋ ከተማ
ጥሩነሽ ዲባባ 0-1 ኢትዮ ንግድ ባንክ
አዳማ ከተማ 3-1 አርባምንጭ ከተማ
ሰኞ ጥር 6 ቀን 2011
አዲስ አበባ ከተማ 10:00 ጌዴኦ ዲላ
_____

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *