ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሲዳማ ቡና ከ ወላይታ ድቻ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሲዳማ ቡና ከ ወላይታ ድቻ

በአንድ ነጥብ የሚበላለጡ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ የ30ኛ ሳምንት ቀዳሚ መርሐግብር ነው።

በአርባ ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች በአንድ ነጥብ ከፍ ብሎ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠውን የነገው ተጋጣሚያቸው ማሸነፍ የደረጃ መሻሻል ያስገኝላቸዋል።

ሲዳማ ቡናዎች በሁለተኛው ዙር ከፍተኛ የደረጃ መሻሻል ያስገኘላቸውን ሁለንተናዊ ለውጥ አምጥተዋል፤ ከውድድር ዓመቱ አጋማሽ በኋላ በተከናወኑ አስር ጨዋታዎች ውስጥ በአንዱ ብቻ ሽንፈት ያስተናገደው ቡድኑ በድሬዳዋ እና አዳማ ከተሞች ከነበረው አሉታዊ አካሄድ መላቀቁን ተከትሎ ከስጋት ቀጠናው በመራቅ በሰንጠረዡ አጋማሽ ተደላድሏል። በድሬዳዋ የመጨረሻ ሳምንት ተከታታት ሽንፈቶች፤ በአዳማ ቆይታው ደግሞ በተከታታይ የአቻ ውጤቶች የታጀበ ጉዞ የነበረው ሲዳማ ቡና በተለይም በማጥቃት ክፍሉ ያመጣው ለውጥ ለቡድኑ ውጤት መሻሻል እንደ ምክንያት ይጠቀሳል። እርግጥ ቡድኑ በከተማው እና በደማቅ ድጋፍ ታጅቦ መጫወቱ ለውጤቱ ማማር የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉ ባይካድም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ያስቆጠረው የፊት መስመር ጥምረቱ ግን የጎላውን ድርሻ ይወስዳል።

የጦና ንቦቹ በሁለተኛው ዙር ላይ ወጥ ብቃት ማሳየት ከከበዳቸው ክለቦች መካከል ይጠቀሳሉ። ቡድኑ መሪው መድንን የገጠመበት ጠንካራ ጨዋታ ጨምሮ ተከታታት አራት ጨዋታዎች ላይ ድል አድርጎ የሁለተኛ ዙር ጉዞውን ቢጀምርም ቀጥለው በተካሄዱ መርሐግብሮች ግን በወጥነት መዝለቅ አልቻለም። በመደዳ ድል ካደረገባቸው ጨዋታዎች በኋላ በተከናወኑ ስድስት መርሐግብሮች ሦስት ሽንፈት፣ አንድ ድል እና ሁለት የአቻ ውጤቶች ማስመዝገቡም የዚህ ማሳያ ነው።

በአርባ አንድ ነጥብ 6ኛ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ ምንም እንኳን በነገው ዕለት ድል ማድረግ ከሁለት በላይ የደረጃ መሻሻል ባያስገኝለትም በቀጠናው ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር ደረጃው እንዳያሽቆለቁል ዳግም ወደ ድል መንገድ መመለስ ግድ ይለዋል። ይህ እንዲሆን ደግሞ በቡድኑ ውጤት አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ የሚገኘው ወጥነት የጎደለው የግብ ማስቆጠር አቅሙ ማሻሻል ይኖርበታል። በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታ ላይ ተጋጣሚያቸው ግብ ከማስቆጠሩ በፊት በነበሩ ደቂቃዎች ይህ ነው የሚባል የጠራ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት የጦና ንቦቹ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም በቀጣይ መርሐግብሮች ግን የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ያላቸውን ድክመት በዘላቂነት የመፍታት ስራ ይጠብቃቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የነገው ተጋጣሚያቸው ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ያስቆጠረ በጥሩ የግብ ማስቆጠር ብቃት ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ የመከላከል አደረጃጀታቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ መሆን ይኖርበታል።

በሲዳማ ቡና በኩል ዮሴፍ ዮሐንስ ከቅጣት ተመልሷል። መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞት የነበረው መስፍን ታፈሰ ጨምሮ የተቀሩት የቡድኑ አባላትም ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በወላይታ ድቻ በኩል በጉዳትና በቅጣት ከነገው ጨዋታ ከሆነው ተከላካዩ ናትናኤል ናሴሮ በስተቀር ሁሉም የቡድኑ ስብስብ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 21 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 2 ጨዋታ ሲያሸንፍ 8 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተው ሲዳማ ቡና 11 ጊዜ አሸንፏል። በሁለቱ ግንኙነት እስካሁን 32 ጎሎች ሲቆጠሩ ወላይታ ድቻ 11 ፣ ሲዳማ ቡና 24 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።