ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ በሊጉ ለመቆየት ተስፋን የምትሰጥ ሦስት ነጥብን አሳክተዋል

ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ በሊጉ ለመቆየት ተስፋን የምትሰጥ ሦስት ነጥብን አሳክተዋል

ምዓም አናብስቶቹ በዓመቱ ዘጠነኛ ድላቸው ሲዳማ ቡናን በቤንጃሚን ኮቴ የግንባር ጎል 1ለ0 በመርታት በሊጉ ለመክረም ተስፋቸውን የምታለመልምላቸውን ሦስት ነጥብ አግኝተዋል።

ከቀናት በፊት መቐለ 70 እንደርታ ከፋሲል ከነማ ጋር 1ለ1 የተለያዩበትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ሲገቡ በመድን የ3ለ0 ሽንፈት በገጠማቸው ሲዳማ ቡና በኩል ግን የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። ቶማስ ኢካራ ፣ ደስታ ደሙ ፣ በዛብህ መለዮ ፣ ሬድዋን ናስር እና መስፍን ታፈሠ ወጥተው መስፍን ሙዜ ፣ ጊት ጋትኩት ፣ ዮሴፍ ዮሐንስ ፣ አቤኔዘር አስፋው እና ሀብታሙ ታደሠ ተክተዋቸው በቋሚነት መግባት ችለዋል።

መቐለ 70 እንደርታ በሊጉ የመቆየት ተስፋቸውን ለማለምለም ሲዳማ ቡናዎች ደረጃቸውን ወደ ሦስት ከፍ ለማድረግ ያደረጉት የሦስተኛ ቀን የሳምንቱ ሁለተኛ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በጥቅሉ ደካማ እንቅስቃሴዎች የነበሩት ነበር። አጫጭር የሆኑ ነገር ግን በየደቂቃው የሚቆራረጡ ቅብብሎች በርክቶ በታየበት ጨዋታ መጠነኛ የአጀማመር መሻሻል የነበራቸው ሲዳማ ቡናዎች 2ኛው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ዮሐንስ በግምት ከሀያ አምስት ሜትር ርቀት አክርሮ መቶ የግብ ዘቡ ሶፎኒያስ ሲመልሳት ከግራ ጠባብ አንግል ሆና ይገዙ ያደረጋት እና በግቡ የውጪው መረብን ነክታ የወጣችበት አጋጣሚ ቡድኑ እንደነበረው ከፍ ያለ አጀማመር የተደረገች ሙከራም ሆናለች።

ቅዝቅዝ ባሉ እንቅስቃሴዎች መጓዙን የቀጠለው ጨዋታ መቐለዎች ከመስመር ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ በሽግግር ለመጫወት ጥረት ያደረጉበት ቢሆንም የመጨረሻ የሜዳ አጠቃቀማቸው ግን ፍፁም በስልነት የታጀበ አልነበረም። ሜዳ ላይ ከነበሩ የኳስ ንክክኪዎች ውጪ ረጅሙን ደቂቃ ሙከራዎች ያልታዩበት ጨዋታ 40ኛው ደቂቃ በመቐለ በኩል መድሀኔ ብርሀኔ ማቀበል የሚችልበትን አማራጭ ይዞ ከግራ ተነስቶ በጥልቀት ይዞ የገባውን ኳስ ሞክሮ መስፍን ሙዜ በቀላሉ የያዘበት ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ግን ቡድኑ እጅግ ያለቀለት አጋጣሚን ፈጥሮ መጠቀም አልቻሉም። ብሩክ ሙሉጌታ ከቀኝ የሜዳው ክፍል ይዞ የገባውን ኳስ ለቦና ዓሊ ሰጥቶት አጥቂው ልታመልጠው የነበረችን ኳስ በሁለተኛው አጋጣሚ ተቆጣጥሮ ቢመታትም ወደ ውጪ ወጥታበታለች በብዙ ረገድ ደካማ  ማጥቃቶች የነበሩት ጨዋታም ያለ ጎል ተገባዷል።

ከዕረፍት መልስ ሲዳማ ቡና ደግፌ አለሙ እና ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃንን ፣ በፍራኦል መንግስቱ እና በበዛብህ መለዮ ቀይረው ቢመለሱም እጅግ ብልጫውን ወስደው ቶሎ ቶሎ በማጥቃት ወጥ የነበሩት ግን ሞዓም አናብስቶቹ ናቸው። በ49ኛው ደቂቃ ሲዳማዎች ለማስጀመር ሲሉ በመቐለ ተጫዋቾች የተነጠቁትን ኳስ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ አሾልኮ ሰጥቶ ብሩክ ሙሉጌታ በደካማ ግራ እግሩ ያደረጋት ሙከራን ያሬድ ባዬ እንደምንም ኳሷን አግዶበታል። በ55ኛው ደቂቃ ያሬድ ከበደ ያደረጋት ጠንካራ ምት መስፍን ሙዜ ሲመልሳት  ብሩክ ሙሉጌታ አግኝቶ ቢያስቆጥረውም አወዛጋቢ በሆነ የዳኝነት ውሳኔ ረዳት ዳኛው ተመስገን ሳሙኤል ከጨዋታ ውጪ በሚል ጎሏን ሽረዋታል።

በተጋጣሚያቸው በእንቅስቃሴም ሆነ በጎል ሙከራ ረገድ ብልጫ የተወሰደባቸው ሲዳማዎች በመልሶ ማጥቃት  57ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ አስቻለው ሙሴ አክርሮ መቶ ሶፎኒያስ ሰይፈ ያወጣት እና ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በሳጥኑ የግራ ክፍል ሀብታሙ ታደሠ ሞክሮ የግብ ዘቡ ሶፎኒያስ እና በግራ ቋሚ ብረቱ ዕገዛ ኳሷ በቀላሉ ልትመክንባቸው ችላለች። ቶሎ ቶሎ ወደ ሳጥን በሚጣሉ እና ከቆሙ ኳሷች አንዳች ነገርን የፈለጉ የሚመስሉት መቐለዎች 64ኛው ደቂቃ ሔኖክ ከቀኝ ወደ ውስጥ አሻግሮ ያሬድ ብርሀኑ በግንባር ገጭቶ መስፍን ከያዘበት ከአራት ደቂቃዎች መልስ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል። ከማዕዘን ምት ሔኖክ አዱኛ ያሻማውን ኳስ መናፍ ዐወልን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ጋናዊው ተከላካይ ቤንጃሚን ኮቴ በግንባር ገጭቶ መረቡ ላይ ኳሷን አሳርፏታል።

ጎልን ካስቆጠሩ በኋላ ወረድ እያሉ በተቃራኒው በተጋጣሚያቸው ጫናዎችን ማስተናገድ የጀመሩት መቐለዎች ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡና በሚታይባቸው አለመረጋጋት የተነሳ ሀብታሙ ታደሠ እና አበባየው ሀጂሶ ያገኟቸውን ነፃ አጋጣሚዎች ያመከኑበት እና መቐለዎች በጭማሪው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ቦና ዓሊ ያለቀለት ዕድልን ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ጨዋታው በመጨረሻም መቐለን 1ለ0 አሸናፊ አድርጎ ተቋጭቷል።

የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ጨዋታው አጀማመሩ ጥሩ ቢመስልም በአጠቃላይ በማጥቃቱ ደካማ መሆናቸውን ለማሸነፍ ፣ ጎልንም ለማስቆጠር ምንም ስሜት በቡድናቸው ውስጥ እንዳልነበር ጠቁመው ፣ በቡድኑ ውስጥ ተጫዋቾች ሙሉ አለመሆናቸውን እንዲሁም ቀጣይ ያለባቸው የጥሎ ማለፍ ጨዋታን እያሰቡ መጫወታቸው ተፅዕኖ ውስጥ እንዳስገባቸው ጠቁመው በዋንጫው ጨዋታ ላይ ማስተካከል እንዳለባቸው በንግግራቸው ተናግረዋል። የመቐለ 70 እንደርታው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በበኩላቸው ተጋጣሚያቸው ካለበት ደረጃ አንፃር ጥሩ መሆኑን በመናገር የዛሬውን ነጥብ ማሳካት አስፈላጊ በመሆኑ ጫና ውስጥ ቡድናቸው ሆኖ ግን ቅድሚያ ለውጤት በመስጠታቸው አሸንፈው መውጣታቸው ደስተኛ እንዳደረጋቸው ገልፀው ስለተሻረችው ጎል ምንም ማለት እንደማይችሉ በጥቅሉ በንግግራቸው ውስጥ አካተዋል።