መረጃዎች | የ12ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን  ጨዋታዎች

መረጃዎች | የ12ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

12ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ መርሐግብሮች ይጠናቀቃል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችንም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

መቻል ከ ኢትዮጵያ ቡና

በ11ኛው ሳምንት መርሐግብር አዳማ ከተማን ሦስት ለአንድ በማሸነፍ ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር የታረቁት መቻሎች መሪዎቹን እግር በእግር ለመከተል የሚያስችላቸውን ድል ለማግኘት ኢትዮጵያ ቡናን ይገጥማሉ። በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ላይ በርከት ያሉ ዕድሎች ፈጥሮ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ከሙሉ ብልጫ ጋር ያሸነፈው ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ በዕለቱ ያሳየውን እንቅስቃሴ በመድገም ተከታታይ ድሉን ለማሳካት እያለመ ወደ ሜዳ ይገባል። በተለይም በተጠቀሰው ጨዋታ ከወትሮ በተለየ ስልነት የቀረበው የፊት መስመር ጥምረት ብቃት ማስቀጠል ከጦሩ ይጠበቃል።

በ 12 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከአሰልጣኝ ዐቢይ ካሳሁን ጋር ከተለያዩ በኋላ ዛሬ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በመጨረሻው መርሐግብር መሪነታቸውን ማስጠበቅ ተስኗቸው በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈት ያስተናገዱት ቡናማዎቹ በሸገር ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ላይ ካሳኳቸው ተከታታይ ድሎች በኋላ ባለፉት ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ከድል ጋር ተራርቀዋል። ከአሰልጣኝ ለውጥ በኋላ በምን አይነት አኳኋን ይቀርባሉ የሚለው ነገር አዳጋች ቢሆንም በተለይም በመጨረሻው ጨዋታ የተስተዋለባቸውን ጉልህ የአፈፃፀም ድክመት ማረም ይኖርባቸዋል።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 36 ጨዋታዎችን አድርገው ኢትዮጵያ ቡና 19 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መቻል 7 ጊዜ ድል አድርጎ በ10 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ቡናማዎቹ 55 ጦሩ ደግሞ 34 ግቦችን አስቆጥረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ኢትዮጵያ መድን

በ 12 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከስጋት ቀጠናው የሚያርቃቸውን ድል ፍለጋ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ በተደረጉ ጨዋታዎች አርባምንጭ ከተማን አሸንፈው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ የተጋሩት ሀምራዊ ለባሾቹ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ከኢትዮጵያ መድን ጋር በሚፋለሙበት ጨዋታ ላይ በርከት ያሉ ለውጦችን ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከምንም በላይ ደግሞ አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ ለሚለው ወጥነት የጎደለው የቡድኑ ብቃት መፍትሔ ማበጀት ይኖርባቸዋል።

በ13 ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ መድኖች ደረጃቸው ለመሻሻል የሚረዳቸው ወሳኝ ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባሉ። በመጨረሻዎቹ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ማሳካት ያልቻለው ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ ድል ማድረግ የሚችል ከሆነ እስከ አራት ደረጃዎች የማሻሻል ዕድል አለው። ይህ እንዲሳካ ግን ከ9ኛ እስከ 11ኛ ሳምንት ድረስ በተካሄዱ ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች የተስተዋለው መሪነትን የማስጠበቅ ድክመት መቅረፍ ይኖርባቸዋል።

ክለቦቹ በታሪካቸው 24 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 10 ፣ ኢትዮጵያ መድን ደግሞ 4 ጊዜ ሲያሸንፉ 10 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ንግድ ባንክ 38፣ መድን ደግሞ 25 ግቦችን አስቆጥረዋል።